የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት 2ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ማጠቃለያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለረጅም ዓመታት ሲያነሳቸው የነበሩ መሠረታዊ ጥያቄዎችን መመለሱን ገልጸዋል።
በዚህም የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሕጋዊነት ችግር ተፈቶ በአዋጅ እንዲቋቋም መደረጉን፣ በተቋሙ ውስጥ የነበረው መለያየት በዕርቀ ሰላም መፈታቱን፣ የእስላማዊ ባንኪንግ አገልግሎት ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን እና በአዲስ አበባ የነጃሺ ማዕከል ግንባታ የሚሆን መሬት መፈቀዱን በአብነት አንስተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እነዚህን የለውጡ ውጤቶች መሠረት በማድረግ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በሀገር ግንባታ ሂደት የበለጠ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በተለይም በሀገር ውስጥ የሚፈጠሩ ልዩነቶች በሰላማዊ ውይይትና በዕርቅ እንዲፈቱ የሃይማኖት መሪዎች ግንባር ቀደም ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ሙስናንና ብልሹ አሠራርን በመታገል፣ ወጣቶችን በበጎ ምግባር በማስተማርና የሥራ ባህልን በማበረታታት ረገድ ጠንክረው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
የመደመር መንግሥት መንፈሳዊነትን እንደ ታላቅ ሀገራዊ ኃይል እንደሚመለከተው ያብራሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሃይማኖት ተቋማት እርስ በእርስ የሚግባባ፣ የሚከባበር እና የሚተዛዘን ማኅበረሰብ በመፍጠር ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በአሸናፊ እንዳለ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: