ከ300 በላይ የብሪክስ አባል ሀገራት የተሳተፉበትና በቻይና በተካሄደው የክህሎት ውድድር፤ 3 ኢትዮጵያዊያን የወርቅ፣ የብርና የነሃስ ሜዳሊያ አሸናፊ መሆናቸውን የፌዴራል ቴክንክና ሙያ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ለ11ኛ ዙር በቻይና ጎዋንዡ በተካሄደው ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ከተወዳደሩ ወጣቶች መካከል፤ ዘላለም እንዳለው 1ኛ ወጥቶ የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ ሀገሩን በዓለም መድረክ ቀዳሚ ማድረጉን የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በተለይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል።
ወጣት ዘላለም እንዳለው የዲጂታል ግብርና መቆጣጠሪያና መከታተያ ሥርዓት ሰርቶ ባቀረበው የፈጠራ ሥራ፤ የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ማድረጉን ነው ዋና ዳይሬክተር የተናገሩት።
2ኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነው ወጣት አቤኔዘር ተከስተ ሲሆን በማንዋል የሚሰራ ፕላስቲክ ቅርጽ የሚያወጣ ማሽን ‘Manual Plastic injection Molding Machine’ በመስራት ሲሆን፤ 3ኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነችው ወጣት ነቢሀ ነስሩ ደግሞ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሰረተ በሆስፒታሎች ታማሚዎች ነርስ ለመጥራት የሚያስችላችው ‘Nurse calling System’ የፈጠራ ሀሳብ ለውድድር አቅርባ አሸናፊ መሆኗ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የሚዘጋጀውን ክህሎት ኢትዮጵያ የሚል የውድድር መረሐ ግብርን አልፈው ወደ ቻይና የሄዱት ወጣቶቹ፤ በሀገር ውስጥ ያደረጉት ውድድር በፈጠራ ሥራቸው ለማሸነፍ እንደረዳቸው ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ወጣቶቹ ያቀረቡትና ያሸነፉበት የፈጠራ ሀሳብ ከውድድር ባሸገር ሰፋ ያለ ልምድና ተሞክሮ የተገኘበት እንደነበርም ገልጸው፤ በቀጣይነት ለሚካሄዱ ውድድሮች አጋዥ እንደሆነም ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል።
የፈጠራ ሀሳቦቹ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በተጨባጭ መሬት ላይ ታይተውና ተፈትሸው ችግር ፈቺ መሆናቸው የተረጋገጠ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በቀጣይነት ወደ ምርት የሚገቡበት ሁኔታ ስለ መኖሩም ጠቁመዋል።
በመሀመድ ፊጣሞ