Search

ቀይ ባሕር የጥንታዊ ሥልጣኔያችን እና የዓለም አቀፍ ግንኙነታችን መሠረት ነው

ዓርብ ኅዳር 04, 2019 116

ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ የንግድ መተላለፊያ ብቻ ሳይሆን የጥንታዊ ሥልጣኔዋ፣ የታሪኳ እና ከተቀረው ዓለም ጋር ለነበራት ዘርፈ ብዙ መስተጋብር ዋነኛ መግቢያ በር ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል።

ታሪካዊ እውነታዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በዘይላ፣ በበርበራ፣ በዳህላክ እና በአሰብ ወደቦች በኩል ከዓለም ሕዝቦች ጋር የባህል፣ የዕውቀት እና የሥልጣኔ ልውውጥ ስታደርግ ቆይታለች። ይህም ቀይ ባሕር ከሀገራችን ታሪካዊ ማንነት ጋር ያለውን ጥልቅ ቁርኝት በግልጽ ያሳያል።

የደጀን ከተማ ነዋሪ የሆኑት ሼህ መሐመድ አህመድ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ እና ባህላዊ እሴቶች በቀጥታ ከቀይ ባሕር ጋር የተሳሰሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

የነጃሺን ታሪክ ጨምሮ በቀይ ባሕር በኩል የተፈጠሩ ታሪካዊ ትስስሮች የማንነታችን መገለጫዎች መሆናቸውን የጠቀሱት ሼህ መሐመድ፣ "ታሪካችን፣ ኢኮኖሚያችን እና ማንነታችን ሙሉ የሚሆነው ተቆርጦ የቀረው የቀይ ባሕር ቁርኝታችን ሲመለስልን ነው" ብለዋል።

የአንዲት ሀገር ታሪክ የሚመዘነው በድንበሯ ስፋት ብቻ ሳይሆን በታሪክ በተጫወተችው ሚና እና በነበሯት ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች ጭምር ነው።

ከሦስት አሥርተ ዓመታት በፊት የባሕር በር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ በፖለቲካዊ ሴራዎች ከባሕሩ መነጠሏ የትናንት ታሪክ ብቻ ሆኖ አልቀረም፤ ይልቁንም ዛሬም በኢኮኖሚዋ፣ በሎጂስቲክስ አቅሟ እና በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል። ከምንም በላይ ደግሞ ቀጣናውን እየተፈታተነ ባለው የደኅንነት ስጋት ውስጥ ጥሏታል።

ሌላኛው የደጀን ከተማ ነዋሪ መርጌታ ይትባረክ ጌቴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ያጣችው ያለምክንያት እና በግፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ "ወደ ባሕር መውጫ ያጣ ሰው መረማመጃ እንዳጣ ይቆጠራል፤ የልማታችን ትልቁ አውታር እሱ ስለሆነ እሱን ለማግኘት ሁላችንም ልናስብበት ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ከንግድ ሸቀጦች ማስተላለፊያነት የላቀ የሉዓላዊነት፣ የኢኮኖሚ ነጻነት እና የህልውና ጥያቄ ነው።

ለውጭ ንግድ እና ለወደብ አገልግሎት በሌሎች ሀገራት ውሳኔ ላይ ብቻ ተመርኩዞ መጓዝ የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚኖረውን አማራጭ የሚገድብ ነው።

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው አቶ ጥላሁን ታዬም ለወደብ ኪራይ የሚከፈለው ከፍተኛ ወጪ የሀገራችንን ኢኮኖሚ እየጎዳ መሆኑን አንስተዋል።

 

አክለውም ሁሉም ዜጋ ይህን ጉዳይ የራሱ አጀንዳ በማድረግ ተረባርቦ ይህንን የህልውና ጥያቄ ማሳካት የማይታለፍ ሀገራዊ ግዴታ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: