Search

አርሶ አደሩ ምርቱን በፍጥነት እንዲሰበስብ ጥሪ ቀረበ

ዓርብ ኅዳር 04, 2019 127

የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት በቀጣይ ቀናት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር አስታውቋል።

ይህንንም ተከትሎም በማሳ ላይ የሚገኙና የደረሱ ሰብሎች በዝናብ ምክንያት እንዳይበላሹና የምርት ብክነት እንዳይከሰት ህብረተሰቡ በተለይም አርሶ አደሩ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የግብርና ሚኒስቴር ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

በኢንስቲትዩቱ ትንበያ መሠረት በቀጣዮቹ ቀናት ዝናብ አዘል የአየር ሁኔታ የሚስተዋልባቸው አካባቢዎች በዋናነት የደቡብ ምዕራብ፣ የደቡብ እና የመካከለኛው ኢትዮጵያ ክፍሎች፣ ሲዳማ፣ እና የሶማሌ ክልሎችን ያካትታል።

በተለይም በኦሮሚያ ክልል ምዕራባዊና ደቡባዊ ዞኖች፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ በሲዳማ እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች መጠነኛ ዝናብ እንደሚጥል የሚጠበቅ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ተመላክቷል።

በሶማሌ ክልል የዳዋ፣ ሊበን፣ አፍዴር፣ ሸበሌ፣ ቆረሂ፣ ዶሎና ነጎብ፣ ጀረር ዞኖች መካከለኛ ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡

የመኸር ወቅት ምርት የሚሰበሰብበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በመሆኑ የሚጥለው ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ የመበስበስ፣ የመብቀልና የጥራት መጓደል አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የአየር ሁኔታውን በንቃት በመከታተል የደረሱ ሰብሎችን ሳይዘገዩ በመሰብሰብና ዝናብ በማይደርስበት ደረቅ ሥፍራ በማከማቸት ምርታቸውን ከጉዳት እንዲታደጉ ተጠይቋል።

ከሰብል ስብሰባው ጎን ለጎን በተለያዩ የግብርና ሥራዎች ላይ የተሰማሩ አካላት እና የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍና መረጃ በወቅቱ እንዲያደርሱ ኢንስቲትዩቱ ጥሪ አቅርቧል።

 

በመሐመድ  ፊጣሞ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: