በሀገር አቀፍ ደረጃ የታቀደውን የ4.5 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እውን ለማድረግ፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ከማምረት ጎን ለጎን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የቤት ፋይናንስ ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ እየተገነቡ የሚገኙ ከ100 ሺህ በላይ የመኖሪያ ቤቶችን የሥራ ሂደት በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት፣ ግዙፉ የቤቶች ልማት መርሐ ግብር የግብዓት አቅርቦትን፣ የፋይናንስ አማራጭንና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ባቀናጀ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል።
ለግንባታው የሚያስፈልጉ እንደ ብረት፣ መስታወት እና ሴራሚክ ያሉ መሠረታዊ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማሳደግ የመንግሥት ቀዳሚ ትኩረት እንደነበርም አስረድተዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ከባንኮች ጋር በመቀናጀት የሞርጌጅ ሥርዓትና ልዩ የፋይናንስ ፈንድ እየተደራጀ መሆኑን ጠቅሰው፣ "ሐውሲንግ ሲገነባ የፋይናንስ ስኪሙ አብሮ ካልተሠራ በስተቀር ሰው በቀላሉ ቤት ስለተሠራ ብቻ ሊገዛ አይችልም፤ እንዴት አድርጎ ያንን ቤት የግሉ ማድረግ እንደሚችልና እየኖረበት እንዴት እንደሚከፍል አብሮ ሊመቻችለት ይገባል" ብለዋል።
በአዲስ አበባ የተጀመሩት ከ100 ሺህ በላይ ቤቶች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ መጠናቀቅ ምዕራፍ መድረሳቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ይህ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲጠናቀቅ ሥራው በሌሎች ከተሞችና በገጠር አካባቢዎች በስፋት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ቃል የገባነውን 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤት በመንግሥት፣ በግል እንዲሁም በመንግሥት እና ግል አጋርነት አስበልጠን እንፈፅማለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: