ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በመቐለ ከተማ ከኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ የትግራይም ሆነ የኢትዮጵያ ዋነኛ የጸጥታ ችግር የዴሞክራሲ ጥያቄ ሳይሆን ኢትዮጵያን በውስጥ ግጭት የማዳከም የረጅም ጊዜ የሻዕቢያ እና ከጀርባው ያሉ ታሪካዊ ጠላቶች እቅድ ውጤት ነው ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ከ2013 ዓ.ም ግጭት በፊት በትግራይ ክልል እንቅስቃሴው ተገድቦ፣ አመራሮቹ ከመቐለ አውሮፕላን ማረፊያ እስከመባረር የደረሰ ተጽዕኖ ሲደርስበት መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከዚያም በኋላ የፌዴራል መንግሥት ለሰላም ዕድል ለመስጠት ሠራዊቱን ከትግራይ ቢያስወጣም በአፋር እና በቆቦ አቅጣጫዎች ሁለተኛና ሦስተኛ ዙር ጦርነቶች መከፈታቸውን ጠቅሰዋል።
ሠራዊቱ ሦስተኛውን ዙር ጦርነት ቀልብሶ ለመቐለ 90 ኪሎ ሜትር ሲቀረው ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሲባል መቆሙን እና ከድንበር አካባቢ ውጪ ያለውን ኃይል ማስወጣቱን ተናግረዋል።
ይሁንና ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ትጥቅ የመፍታትና ተፈናቃዮችን የመመለስ ሂደት መስተጓጎሉን የጠቀሱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፣ የጌታቸው ረዳን ጊዜያዊ አስተዳደር ማኅተምና ቁልፍ ከመንጠቅ አልፎ በሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ ላይም መፈንቅለ መንግሥት መፈጸሙን ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግሥት ጦርነትን ለማስቀረት ይህን ሁሉ በትዕግሥት ቢያልፍም፣ በሻዕቢያ አስተባባሪነት ከፋኖ፣ ከሸኔ እንዲሁም ከሱዳን እና ከግብጽ ጋር በመመካከር “ጽምዶ” የተሰኘ ጥምረት ተፈጥሮ አራተኛ ዙር ወረራ መፈጸሙን አብራርተዋል።
በዚህም መከላከያ ሠራዊት እንደ ቀድሞው ትግራይ አንገባም ብሎ መቆም ተገቢ አለመሆኑን በማመን፣ ወራሪ ኃይልን ከትግራይ አስወጥቶ እስከ ኤርትራ ድንበር ማድረሱን አስታውቀዋል።
ጦርነቱን ከፍተው የተሸነፉ አካላት በአሁኑ ወቅት አዲኳላ፣ መንደፈራ እና አስመራ እንደሚገኙ የጠቆሙት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ብርሃኑ ጁላ፣ ከጀርባ ያሉ ታሪካዊ ጠላቶች ዋና ዓላማ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ በማባላት በቀጣናው ተፎካካሪ ኃያል ሀገር እንዳይፈጠር ማድረግ መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: