Search

በኅብረት የጸናችው ኢትዮጵያ

ዓርብ ኅዳር 04, 2019 131

የዲፕሎማሲ ስኬት፣ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እና ዓለም አቀፍ ተደማጭነት ከሜዳ የሚገኝ ሳይሆን፣ በሀገር ውስጥ በሚኖረው በኅብረት የጸና ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም ነው። 

ኢትዮጵያ ዛሬ በአፍሪካ ቀንድና በዓለም አቀፍ መድረኮች በተለይም በኮፕ32 ዝግጅት እና በባሕር በር ዲፕሎማሲ ላይ እየተጫወተች ያለው ሚና እና ስኬት ከኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ ጥንካሬ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ነው።

የውጭ ኃይሎች ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት የሚወስኑት ባላት የውስጥ መረጋጋት እና በሕዝብና በመንግሥት ጽኑ ቁርጠኝነት ነው።

ሕዝብ እና መንግሥት በአንድ ሀገራዊ አጀንዳ ዙሪያ በኅብረት ሲቆሙ፣ የውጭ ግፊቶችን የመቋቋም እና ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር አቅም በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል፤ ተቀናቃኞችም ሆኑ አጋሮች ኢትዮጵያን የሚመለከቷት በብሔራዊ ዓላማ ጸንታ የቆመች ሀገር አድርገው ነው።

ኢትዮጵያ በውስጣዊ ርብርብና በሕዝባዊ ንቅናቄ በአረንጓዴ ዐሻራ እና በንጹህ ኢነርጂ ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ግዙፉን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ እንድታዘጋጅ አስችሏታል።

በተመሳሳይ የባሕር በር ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ለአፍሪካ ቀንድ እና ለዓለም ለማሳወቅ የውስጥ መተማመን እና አንድነት መሠረታዊ ነጥብ ነው።

የቀጣናውን ሰላም እና የንግድ ደኅንነት ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ያላት ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ ከጸና ውስጣዊ አንድነት ጋር ሲደመር የማይበገር አቅም ይፈጥራል።

ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚደረጉ የውጭ ሸፍጦች እና የነጣጣይ ትርክት ጦርነቶች የሚከሸፉት በዘመናዊ የዲፕሎማሲ ስልት ብቻ ሳይሆን፣ የኅብረ ብሔራዊ አንድነቱ ማዕቀፍ ጠንክሮ ሲገኝ ነው።

ብዝኃነቷን በዴሞክራሲያዊ መንገድ አስተባብራ በጋራ ልማት ራሷን እየለወጠች ያለችው ኢትዮጵያ፣ በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ መድረክ የማትበገር ሀገር ሆና ትቀጥላለች።

 

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: