የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጋራ የሚያዘጋጁት አምስተኛው ምዕራፍ የነጋድራስ የሥራ ፈጠራ ውድድር የፍጻሜ መርሐ ግብር በመጪው እሁድ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።
ኢቢሲ እንደ ሀገራዊ የሚዲያ ተቋም የወጣቶችንና የፈጠራ ባለሙያዎችን አቅም ለማውጣት፣ ለሥራ ፈጣሪዎች ሰፊ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን በመስጠት እና ሀሳባቸውን ለገበያ እንዲያስተዋውቁ በማድረግ ዘርፉን በልዩ ትኩረት እያበረታታ ይገኛል።
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመጣመር የሚዘጋጀው ይህ ውድድርም ሀሳብ ኖሯቸው የፋይናንስና የገበያ ትስስር ለሚቸገሩ ዜጎች ትልቅ ድልድይ ሆኖ እያገለገለ ነው።
ባለፉት አራት ምዕራፎች 1መቶ 20 የተለያዩ የሥራ ፈጠራ ፕሮጀክቶችን ያወዳደረው ነጋድራስ በአምስተኛ ምዕራፍ ለፍጻሜ የደረሱ አምስት ተወዳዳሪዎችን በአጠቃላይ የ2 ሚሊዮን ብር ሽልማት አዘጋጅቶላቸዋል።
1ኛ የሚወጣው ወይም የምትወጣው 1ሚሊየን ብር ፣ 2ተኛ 500 ሺህ ብር ፣ 3ኛ 300 ሺህ ብር እንዲሁም 4ኛ እና 5ኛ ለሚወጡት ለእያንዳንዳቸው 100 ሺህ ብር ይሸለማሉ።
ከገንዘብ ሽልማቱ በተጨማሪ፣ ተወዳዳሪዎቹ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ብድር ማመቻቸት አገልግሎት ይሰጣቸዋል።
ኢቢሲ ለሀገር በቀል ፈጠራና ለሥራ ፈጣሪዎች የሚሰጠውን ልዩ ትኩረት በማጠናከር፣ ይህንን የፍጻሜ ውድድር መጪው እሁድ ከቀኑ ዘጠን ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፣ በመዝናኛ ቻናል እንዲሁም በተቋሙ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ለተመልካቾች ያደርሳል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: