Search

በሌት ተቀን ሥራ የተለወጠችው አዲስ አበባ ለአፍሪካ ከተሞች አርአያ እየሆነች ነው

ረቡዕ ኅዳር 16, 2019 44

አዲስ አበባ እ.ኤ.አ. በ2026 የዩኤን ሃቢታት የሻንግሃይ ዓለም አቀፍ የዘላቂ ከተማ ልማት ሽልማት አሸናፊ ከሆኑ አምስት ከተሞች አንዷ ነች።

ከ34 ሀገራት በቀረቡ 92 ማመልከቻዎች መካከል ከኢስታንቡል፣ ከሳንቲያጎ ደ ካሊ፣ ከጂንግዴጀንና ከካቶቪስ ጋር አሸንፋለች። 'ዩኤን ሃቢታት' የቤት፣ የአረንጓዴ መሠረተ ልማት፣ የወንዝ ማገገም፣ የደኅንነቱ የተጠበቀ ትራንስፖርት እና የአሳታፊ አስተዳደር የተቀናጀ አካሄዷን አድንቋል።

የለውጡ መሠረት የፋይናንስ አቅም ነው። በከተማ አስተዳደሩ መረጃ መሠረት በ2018 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ፌዴራል ድጎማ 350 ቢሊዮን ብር በጀት ጸድቋል።

ለ2019 በጀት ዓመት የጸደቀው 502.27 ቢሊዮን ብር ደግሞ የ43 በመቶ ጭማሪ አለው፤ 71.5 በመቶው ለካፒታል ልማት ተመድቧል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ከተማዋ ከ1.3 ትሪሊዮን ብር በላይ የካፒታል ኢንቨስትመንት መሳቧን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለከተማው ምክር ቤት አቅርበዋል።

በጀቱን ወደ ተግባር የለወጠው የአመራር ቁርጠኝነት ነው። ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተሞች ለኑሮ ምቹ፣ አረንጓዴ እና ደኅንነታቸው የተጠበቁ መሆን አለባቸው የሚል ራዕይ ይዘው፣ ሥራውን በአካል እየተከታተሉ የ24/7 የሥራ ባህልን አስተዋውቀዋል፡፡ መሐንዲሶች፣ ተቋራጮች እና ወጣቶች በፈረቃ ይሠራሉ።

በ2017 በጀት ዓመት ከዕቅዱ 95 በመቶ ተፈጽሞ ወደ 16 ሺህ ማኅበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶች አገልግሎት ጀምረዋል፤ 1 ሺህ 392 ኪሎ ሜትር መንገድም ተገንብቷል ወይም ታድሷል።

በ2018 በጀት ዓመትም አፈጻጸሙ ከፍተኛ ነበረ። ከንቲባዋ እ.አ.አ. በ2024 ከ58 ሀገራት ከ216 በላይ ማመልከቻዎች በቀረቡበት የሴኡል 'ስማርት' ከተማ ሽልማት የአመራር ዘርፍ አሸንፈዋል።

ልማቱ ወደ ነዋሪው ሕይወት ተመልሷል፤ ቤት የዚህ ዋነኛው ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በቀጣዮቹ አምስት እስከ ስድስት ዓመታት ቢያንስ 1.5 ሚሊዮን ቤቶች ለመገንባት ባቀደው ልማት አካል፣ አዲስ አበባ የቤት አቅርቦቷን እያሰፋች ነው።

በከንቲባዋ ሪፖርት መሠረት ባለፉት አምስት ዓመታት የከተማዋ የቤት አቅርቦት የግል ዘርፍ ተሳትፎን ጨምሮ እንዲፋጠን እየተሠራ ነው፡፡

1 ሚሊዮን ገደማ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቁርስ እና ምሳ ይመገባሉ፤ ምገባው ከ16 ሺህ በላይ ሰዎች፣ በተለይም ለሴቶች፣ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ፕሮግራሙ እ.አ.አ በ2022 ከ133 ከተሞች መካከል የሚላን የከተሞች የምግብ ፖሊሲ ስምምነት ሽልማትን አስገኝቷል፡፡ በዚያ ዓመት ከአፍሪካ ከተሞች ብቸኛዋ አሸናፊ አዲስ አበባ ነበረች።

የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ብቻ ሳይሆን፣ አሠራሯንም ቀይሯል፤ የውኃ፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም መስመሮች ተቀናጅተው በመዘርጋታቸው ተደጋጋሚ የጥገና ወጪን እና ብክነትን ለመቀነስ አስችሏል።

ለዘመናት የቆሻሻ እና የበሽታ ምንጭ የነበሩ ወንዞች የጎርፍ መከላከያ፣ ድልድይ፣ የእግርና የብስክሌት መንገድ ተሠርቶላቸው ወደ መናፈሻነት እየተቀየሩ ሲሆን፣ አረጋውያን፣ ሕፃናት እና ወጣቶች የሚገለገሉባቸው ስፍራዎች ተበራክተዋል።

አዲስ አበባ እ.አ.አ. በ2023 የአፍሪካ ከንቲባዎች የአመራር ኢኒሼቲቭ (AMALI) ስብሰባን አስተናግዳለች፡፡ ጥቅምት 2026 ደግሞ የኢኒሼቲቩን የአመራር መድረክ ከቢሾፍቱ ጋር በጋራ አዘጋጅታለች።

ከተማዋ እ.አ.አ በ2027 የሚካሄደውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ለማስተናገድ እየተዘጋጀች ነው፡፡ ከታላላቅ የዓለም ከተሞች ጋር ያላትን የእህትማማች ከተሞች ትብብርም እያሰፋች ነው።

የአፍሪካ ከተሞች ዓይናቸውን ወደ አዲስ አበባ የሚያዞሩት በሽልማት ብቻ አይደለም፤ ራዕይ በጽኑ አመራር፣ በጀት በተግባር፣ ሥራ በሌት ተቀን ባህል ሲተረጎም በማየታቸው ነው።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: