የኢትዮጵያን ብዝኃነት እንደ መለያያ ምክንያት ሳይሆን እንደ ትልቅ ጸጋ በመውሰድ ወደ ሀገራዊ አቅም መለወጥ እንደሚገባ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ማንነቶች የሚከበሩባት እና ብዝኃነት በክብር የሚስተናገድባት ኢትዮጵያ እየተገነባች መሆኗን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ባህሎች እና ቋንቋዎች ሰላምን የማጽናት አቅም እንዳላቸው የጠቀሱት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፣ ለልማት እና ለብልጽግና መሠረት የሆኑ የሥራ፣ የመነሳሳት እና የጀግንነት እሴቶችን በአግባቡ በማደራጀት ለሀገር ሥልጣኔ ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
"ጥቃቅን ክሮች ተጠላልፈው ኃያል ገመድ እንደሚፈጥሩ ሁሉ፣ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ እምነቶችና ባህሎች በፍትሕ፣ በጋራ ተጠቃሚነትና በአካታች ብሔራዊ ትርክት ሲተሳሰሩ የማይበገር ሀገራዊ አቅምና ጂኦ-ፖለቲካዊ ልዕልና ይገነባሉ" ብለዋል።
የአንድ ሀገር እውነተኛ ጥንካሬ የሚለካው በዜጎቿ የማንነት መመሳሰል ሳይሆን፣ የተለያዩ ማንነቶችን፣ እሴቶችን እና ታሪኮችን ለጋራ ዓላማ በማቀናጀት መሆኑንም አብራርተዋል።
ብዝኃነት ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ሀብት ቢሆንም በአግባቡ ካልተመራ የሀገርን ጉልበት ሊያባክን እንደሚችል ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።
የመደመር እሳቤም ልዩነቶችን በማጥፋት ሳይሆን በክብር በመያዝ፣ በጋራ ህብርና በተቋማዊ ፍትሕ አንድ ጠንካራ ሀገራዊ ኃይል ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
የዚህ ትውልድ ዋነኛ ኃላፊነትም ያለንን ብዝኃነትና ሀብት በጥበብ በማደራጀት ምርታማ እና ተቋማዊ አቅምን መገንባት ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፣ ሉዓላዊነትን እና አንድነትን ጠብቆ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣይ ትውልድ ማስረከብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: