Search

በቅድመ ሙስና መከላከል ሥራ 12 ቢሊዮን ብር ማዳን ተቻለ

ረቡዕ ኅዳር 16, 2019 54

በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ሙስናን አስቀድሞ ለመከላከል በተሠራው ሥራ 12 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል።

23ኛውን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን አስመልክቶ የኮሚሽኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ቀኑ "ስውር ትሥሥሮችን በማጋለጥ የሙስና ወለድ ወንጀሎችን ሰንሰለት እንበጥስ" በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ገልጸዋል።

ሙስና በሀገር ሀብት ላይ ከሚያደርሰው ኪሳራ ባለፈ ለድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ምክንያት እየሆነ መምጣቱም ተገልጿል።

በተለይም ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ በመሠረታዊ የግለሰቦች መረጃ ላይ የሚፈጸም የሰነድ ማጭበርበር፣ በወጪና ገቢ ንግድ ሥራዎች መረጃን የመደበቅ ተግባራት፣ እንዲሁም በድንበርና በፍተሻ ጣቢያዎች የሚፈጸሙ ስውር የሙስና ወንጀሎች ለማሳያነት ከተጠቀሱት መካከል ናቸው።

ኮሚሽኑሙስናን ለመከላከል ግለሰቦችና ተቋማት ለሙስና ተጋላጭ የሚያደርጉ አሠራሮችን አስቀድሞ መለየትና መከላከል፣ ሙስና ሲፈጸምም ጥቆማ መስጠትና ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

የሕዝብን እምነት ለማጠናከርና ሙስናን ለመታገል የሕግና የተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ የሀብት ማስመለስ አዋጅ፣ ግልጽ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት፣ ዲጂታል የግዥ አሠራር፣ የሙስና ጥቆማ ማቅረቢያ ሥርዓትና የባለሥልጣናት ሀብት ምዝገባ እየተከናወኑ ካሉ የለውጥ ሥራዎች መካከል መሆናቸውን ተገልጿል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ታኅሣሥ 9 የሚከበረው የፀረ ሙስና ቀን በኢትዮጵያም ከኅዳር 1 ጀምሮ እስከ ኅዳር 30 በተለያዩ የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሐ ግብሮች እየተካሄደ መሆኑ ተመላክቷል።

በዘሃራ መሃመድ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: