በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ እና በቶኪዮ 2025 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነችው ኬንያዊቷ አትሌት ቢያትሪስ ቼቤት፣ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ሰፊ ቆይታ አድርጋለች።
በ5 ሺህ ሜትር፣ በ10 ሺህ ሜትር እና በ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የዓለም ክብረ ወሰኖችን በእጇ የጨበጠችው አትሌቷ፣ በቆይታዋ ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጋር ስላላት ወዳጅነት፣ ስለ ቀጣይ ዕቅዷ እና ስለ አፍሪካ አትሌቲክስ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አንስታለች።
ከመም ላይ ፉክክር ባሻገር ያለው ወዳጅነት
በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ መድረኮች በኢትዮጵያውያን እና በኬንያውያን አትሌቶች መካከል የሚደረገው ፉክክር እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ከመም ውጭ ግን ጠንካራ ጓደኝነት እንዳላቸው ቼቤት ገልጻለች። «ጥሩ ጓደኛሞች ነን ማለት እችላለሁ፤ ከውድድር በፊት እንኳን ተገናኝተን አንዳችን ለአንዳችን መልካም ዕድል እንመኛለን» ያለችው ቼቤት፣ በተለይ ከጉዳፍ ፀጋዬ እና ከመዲና ዒሳ ጋር አብዛኛውን ጊዜ እንደምታወራና የቅርብ ጓደኞቿ እንደሆኑ ተናግራለች። በመም ላይ ጠንካራ ፉክክር ቢኖርም፣ ከሩጫው ባሻገር ከተለያዩ ሀገራት በመምጣት የፈጠሩት ወዳጅነት እንደሚያስደስታት አክላለች።
የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የአሸናፊነት ሥነ ልቦና
ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች እጅ የነበሩትን የ5 ሺህ እና የ10 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰኖች ለመስበር የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጥንካሬ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገላት ቼቤት ተናግራለች። «ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች በጣም ጠንካሮች ናቸው፤ ለውድድር ያላቸው ጠንካራ ሥነ ልቦና እና አንድን ነገር ሲፈልጉ ለማሳካት የሚያደርጉት ጥረት ከእነርሱ የተማርኩትና በይበልጥ ያነሳሳኝ ጉዳይ ነው» ስትል አድናቆቷን ገልጻለች።
ለተተኪዎች የተላለፈ መልዕክት
በአሁኑ ወቅት ከልጇ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ከውድድር ርቃ የምትገኘው የ26 ዓመቷ አትሌት፣ በመጪው ጥር ወር ወደ ልምምድ ተመልሳ ጠንክራ ለመቅረብ እንዳቀደች አስታውቃለች።
እንደ እርሷ ስኬታማ ለመሆን ለሚያልሙ ወጣትና ተተኪ አትሌቶች ባስተላለፈችው መልዕክትም፣ ስኬት በትዕግሥትና በሂደት የሚመጣ መሆኑን አሳስባለች። «ለወጣት አትሌቶች የምለው ጊዜያቸውን ወስደው በእርጋታ እንዲጓዙ ነው፤ መቸኮል አያስፈልግም» ያለችው ቼቤት፣ ከታዳጊነት ወደ ወጣትነት ደረጃ በደረጃ ማደግ እንጂ በአንድ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን መቸኮል እንደማይገባ መክራለች። ጉዞዋ ቀላል እንዳልነበር በማስታወስም፣ ጠንካራ ሥነ ልቦና፣ ዲሲፕሊን እና ድጋፍ ካለ ማንኛውንም ዓላማ ማሳካት እንደሚቻል ጠቁማለች።
የአፍሪካ አትሌቲክስ መሠረተ ልማት እና የ2029ኙ ታላቅ ዕድል
ምሥራቅ አፍሪካ በረጅም ርቀት ያላትን የበላይነት በአጭርና በመካከለኛ ርቀቶችም ለመድገም ለአትሌቶች በቂ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ቼቤት ተናግራለች።
የረጅም ርቀት ሯጮች በጎዳና ላይ በመለማመድ ውጤታማ ሊሆኑ ቢችሉም፣ የአጭር ርቀት ሯጮች ግን ዘመናዊ የመለማመጃ መሠረተ ልማቶች እና ጠንካራ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አስረድታለች።
በመጨረሻም አፍሪካ እንደ ዓለም ሻምፒዮና እና ኦሊምፒክ ያሉ ታላላቅ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም እንዳላት የገለጸችው ቼቤት፣ ለዚህም መሠረተ ልማቶችን እና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ማሻሻል እንደሚገባ ጠቁማለች። ኬንያ በ2029 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ማስተናገዷ በሀገሯ ህዝብ ፊት ለመሮጥ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርላት ገልጻ፣ ይህም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ወደፊት ኦሊምፒክን ጨምሮ ታላላቅ ውድድሮችን እንዲያስተናግዱ በር እንደሚከፍት ያላትን ተስፋ አጋርታለች።
በይበልጣል ሰውነት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: