Search

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነገ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የመደመር መንግሥትን የ2019 አቅጣጫ ላይ ማብራሪያ ይሰጣሉ

ረቡዕ ኅዳር 16, 2019 27

የ7ኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ነገ ኅዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

ማብራሪያቸው መነሻ የሚያደርገው ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ያቀረቡትን የ2019 በጀት ዓመት የመንግሥት ዕቅድ ነው፡፡

ዘንድሮ ደግሞ በ7ኛው ምክር ቤት ለሁለተኛ የሥራ ዘመን ተሹመው የመደመር ካቢኔያቸውን ካዋቀሩ በኋላ ለምክር ቤቱ የሚገኙበት የመጀመሪያ ጉባኤ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መንግሥት በቀጣይ ትኩረት የሚያደርግባቸውን አቅጣጫዎች በግልጽ እንደሚያስቀምጡ ይጠበቃል፡፡

በአዲሱ በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የተከናወኑ ሥራዎችን እና የተገኙ ውጤቶችንም ያብራራሉ፡፡

ምክር ቤቱ የመንግሥትን አቋም ካዳመጠ በኋላ የፕሬዚዳንቱን ንግግር እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል፡፡

በጉባኤው በአዲስ አበባ የሚገኙ የሀገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በክብር እንግድነት ይታደማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሁሉም የዶትስትሪም እና መደበኛ የሥርጭት አማራጮች የጉባኤውን ሂደት በቀጥታ ሥርጭት ለሕዝብ ያደርሳል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: