Search

ዓለምን ወደ መሶባችን የሚጠራው የኢትዮጵያ ጣዕም ወደ ገቢ ሊቀየር ይገባል

ረቡዕ ኅዳር 16, 2019 34

ኢትዮጵያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ባህላዊ ምግቦች ባለቤት ናት። ከ76 በላይ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች ቤት የሆነችው ሀገራችን እያንዳንዱ አካባቢ የራሱ ጣዕም፣ አዘገጃጀት እና የአቀራረብ ሥርዓት አለው።

የአመጋገብ ባህላችንም ከምግብነት ባለፈ ጥልቅ ማኅበራዊ እሴት ይዟል። በአንድ መሶብ ዙሪያ ተሰባስቦ በእጅ መመገብ እና መጎራረስ ፍቅርን፣ አብሮነትን እና እንግዳ ተቀባይነትን ይገልጻል። ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም ልዩ የሚያደርጋት ተወዳጅ እሴትም ይኸው ነው።

ዓለምም ይህን ጣዕም ይመሰክራል። ሲኤንኤን ትራቭል ባወጣው "የኢትዮጵያ 15 ምርጥ ምግቦች" ዘገባ ጥብስ፣ ክትፎ፣ ዶሮ ወጥ፣ በየዓይነቱ፣ ተጋቢኖ ሽሮ፣ ጥሕሎ፣ ዱለት፣ ጥሬ ሥጋ፣ ፈጢራ፣ እንቁላል ፍርፍር፣ ዳቦ ፍርፍር፣ ፉል፣ ዓሣ ጥብስ፣ ስፕሪስ እና ፓስታ በእንጀራ ተዋውቀዋል። ዘገባው የኢትዮጵያ ቡናንም ከምግብ በኋላ የግድ ሊቀመስ የሚገባ መጠጥ አድርጎ ጠቅሶታል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚዘወተሩ ሌሎች ምግቦችም የምግብ ባህላችንን ስፋት ያሳያሉ። በኦሮሞ ባህል አንጮቴ፣ ጮሮርሳ፣ ጩምቦ፣ ጩኮና ቆሪ ይታወቃሉ። ጨጨብሳ በምጣድ የተጋገረ ቂጣ በንጥር ቅቤ እና በርበሬ ተለውሶ ከማር ጋር የሚቀርብ ምግብ ነው።

ከገብስ፣ ከስንዴ ወይም ከበቆሎ ዱቄት የሚዘጋጀው ገንፎ በንጥር ቅቤ፣ በበርበሬ እና በእርጎ ይበላል። ቆጮና ቡላ ከእንሰት ተክል የሚዘጋጁ ሲሆን ቡላ ከቅቤና ከአይብ ጋር ይቀርባል።

ረቡዕና ዓርብ የመጾም ባህላችን ደግሞ ሽሮ፣ ምስር ወጥ እና በየዓይነቱን የመሰሉ ከእንስሳት ተዋጽኦ የጸዱ ምግቦችን አበልጽጓል፡፡ ይህም ተክል ተኮር ምግብ ለሚመርጡ ጎብኚዎች ልዩ መስህብ ነው።

ይህ ሀብት ከቱሪዝም አፈጻጸማችን አንጻር ሰፊ ዕድል አለው። በ2018 በጀት ዓመት ከ1.4 ሚሊዮን በላይ የውጭ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡ ዘርፉ 5.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንዳስገኘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል።

እ.አ.አ በ2025 የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ቁጥር በ15 በመቶ አድጓል። ተመድ ቱሪዝም በዓለም ደረጃ ከቱሪዝም ወጪ ከአንድ አምስተኛ በላይ በምግብ ባህል ላይ እንደሚውል ይገምታል።

ይህ የሚያሳየው ጎብኚው ገንዘቡን በመስህብ ብቻ ሳይሆን በሚቀምሰው ጣዕም ላይም እንደሚያውል ነው። በርካታ የአፍሪካ ሀገራትም ይህን እየተገነዘቡ ነው፤ ሦስተኛውን የአፍሪካ የምግብ ቱሪዝም መድረክ ከዲሴምበር 2 እስከ 4 ቀን 2026 በሴራሊዮን ይካሄዳል።

ይህን አቅም ወደ ገቢ ለመቀየር የምግቦቹን አዘገጃጀት እና ታሪካዊ ዳራ ለጎብኚ በሚስብ መንገድ ማቅረብ፣ ባህላዊ የምግብ ኤግዚቢሽኖችን እና ፌስቲቫሎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል።

መንግሥት ያስጀመረውን "Visit Ethiopia" ዲጂታል መድረክ ጨምሮ በዓለም አቀፍ ዲጂታል መድረኮች ምግብን እንደ ራሱን የቻለ መስህብ ማስተዋወቅም ወሳኝ ነው።

በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ባህላዊ ይዘታቸውን ሳይለቅቁ ዓለም አቀፍ የአቀራረብ፣ የንጽህና እና የምግብ ደኅንነት ደረጃ የሚጠብቁ ምግብ ቤቶችን ማስፋፋትም ተመሳሳይ ቦታ አለው።

ከጤፍ፣ ከእንሰት እና ከቅመማ ቅመም አምራች አርሶ አደሮች እስከ ምግብ ቤቱ ያለውን ሰንሰለት ማስተሳሰር ደግሞ ጥቅሙ ከከተማ አልፎ ወደ አምራቹ ማኅበረሰብ እንዲደርስ ያደርጋል።

ባህላዊ ምግቦቻችን የማንነታችን መገለጫ ብቻ አይደሉም፤ ዓለምን ወደ ኢትዮጵያ የሚጋብዙ ታላላቅ የቱሪዝም መስህቦችም ናቸው።

ይህን ሀብት በአግባቡ ካስተዋወቅን እና ካደራጀን መሶባችን ዓለምን ከመጋበዝ አልፎ ለኢኮኖሚያችንም ገበታ ይሆናል።

በመሐመድ ፊጣሞ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: