በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ተቋርጦ የነበረው የነዳጅ አቅርቦት ዳግም መጀመሩ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪንና የሸቀጦች ዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ትልቅ እፎይታ እንደፈጠረላቸው የከተማዋ የታክሲ አሽከርካሪዎች እና የነዳጅ ማደያ ሰራተኞች ገለጹ።
የክልሉ ባለአደራ አስተዳደር ከፌዴራል መንግሥት ጋር በፈጠረው ቅንጅታዊ አሠራር የተነሳ በከተማዋ ተቋርጦ የነበረው የነዳጅ አቅርቦት ችግር ተቀርፎ አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ገብቷል።
ቀደም ሲል ህገወጡ የህወሓት ቡድን መሠረታዊ አገልግሎቶችን በማስተጓጎሉ ምክንያት ሕብረተሰቡ ለከፍተኛ እንግልት ተዳርጎ መቆየቱ ይታወሳል።
በዚሁም ኢቲቪ ነዳጅ ሲሞሉ ያገኛቸው የመቐለ ከተማ አሽከርካሪዎች የነዳጅ እጥረቱ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ባሳደረው ጫና ምክንያት የአገልግሎት ታሪፍ እስከ መቶ እና ሃምሳ ብር ጭማሪ ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ የነዳጅ አቅርቦት በመጀመሩ ታሪፉን ወደ መደበኛው ዋጋ በመመለስ ሕብረተሰቡን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በከተማዋ የነዳጅ አቅርቦት መጀመር ከጅቡቲና ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ሸቀጦች ወደ ክልሉ በቀላሉ እንዲገቡ በማድረግ የሥራ እንቅስቃሴውን እንደሚያነቃቃና የገበያ መረጋጋትን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የነዳጅ ማደያ ሠራተኞች በበኩላቸው በነዳጅ እጥረቱ ምክንያት ሥራቸው ተስተጓጉሎ መቆየቱን አስታውሰው፣ አሁን ላይ ለሕብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የተጀመረው የነዳጅ አቅርቦት ሳይቆራረጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: