ሐላላ ኬላ ያለ ሲሚንቶ እና ያለ ዘመናዊ ማሽን ድንጋይን በድንጋይ ላይ በጥንቃቄ በማነባበር በሀገር በቀል ዕውቀት የተሠራ ግዙፍ ጥንታዊ የመከላከያ ግንብ ነው።
ይህ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን የሚገኘው ግንብ ግዛትን ለመጠበቅ እና አካባቢው ከጥቃት ለመከላከል የተገነባ ሲሆን፣ የትውልዶች ቅብብሎሽ፣ የጽናት እና የጋራ ሥራ ምስክር ሆኖ ይጠቀሳል።
የግንቡ ስፋት እና አሠራር የጥንት የምህንድስና ብቃትን ያሳያል። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የአንድ ረድፍ ርዝመት ከ150 እስከ 200 ኪሎ ሜትር ይገመታል፤ በሰባት ረድፍ አጠቃለይ ርዝመቱ 1 ሺህ 225 ኪ.ሜ የሚሸፍን ሲሆን፣ ከ2.5 እስከ 5 ሜትር ስፋትና ከ2.5 እስከ 3.8 ሜትር በላይ ከፍታ እንዳለው የታሪክ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።
ድንጋዮቹ ያለ ማጣበቂያ እርስ በርስ ተቆራኝተው እና ተደጋግፈው መቆየታቸው የአካባቢውን የመሬት አቀማመጥ እና የድንጋይ ባሕሪ የተረዳ ጥበብ መኖሩን ያረጋግጣል።
የሀላላ ካብ በ1 ሺህ 532 ዓ.ም በዳውሮ የመጀመሪያ ንጉሥ ሥራው ተጀምሮ እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን ዳውሮን ያስተዳድሩ በነበሩ 14 ነገሥታት በቅብብሎሽ የተገነባ እንደሆነ ይነገራል።
አጠቃላይ የግንባታ ሂደቱ 350 ዓመታት የወሰደ ሲሆን፣ በንጉሥ ካዎ ሀላላ መጠሪያ "ሀላላ ኬላ" የሚል ስያሜን አግኝቷል። ትርጓሜውም "ሃላላ" የንጉሡ ስም ሲሆን “ኬላ” የሚለው ደግሞ የድንጋይ ካብ ማለት ነው።
ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ደግሞ ከነገ የሚያስተሳስረው የመደመር ዕሳቤ ይህንን የሀገራችን ቅርስ፣ በ"ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት" ገንብቶ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ጎብኚዎች ምቹ የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ለነገ እንዲሸጋገር አድርጓል።
ይህ ታሪካዊው የሐላላ ግንብ በነገሥታት እና ትውልዶች ድርሻ የተከናወነ በመሆኑ ታላላቅ ሥራዎች በአንድ ጊዜ ወይም በአንድ ትውልድ ብቻ እንደማይጠናቀቁ ማሳያ ነው።
በዚህም ከሐላላ ኬላ የሚገኘው ዋነኛ ትምህርት ቅብብሎሽ ነው። አመራሮች ቢቀያየሩም የልማት እና የመሠረተ ልማት ውጥኖች ሳይቋረጡ ከአንዱ ዘመን ወደ ቀጣዩ በተቋማዊ ቅብብሎሽ መሸጋገር አለባቸው።
የኃይል፣ የመሠረተ ልማት እና የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች በሕግ እና በተቋማዊ አሠራር ሲደገፉ፣ ኢትዮጵያ ትልልቅ ዕቅዶችን የመፈጸም አቅሟ ይጠናከራል።
የነገሥታቱን ዐሻራ ተከትሎ ጊቤ ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የፈጠረውን ሰው ሠራሽ ኃይቅ መነሻ በማድረግ በ"ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት" የተገነባው የሐላላ ኬላ ሪዞርት ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ጎብኚዎች ታሪክ እና የተፈጥሮን በአንድ ቦታ ይዞ ይጠብቃቸዋል።
ከትናንት ወረትን ደምሮ ዛሬን የሚሠራው የመደመር መንግሥት፣ ሐላላ ኬላን የታሪክ ምስክርነቱን እንደያዘ የቱሪዝም መዳረሻነቱን አጉልቷል።
የቀደሙ አባቶችን ፈለግ ተከትሎ የተሠራው ሐላላ ኬላ ሪዞርት ለቱሪዝም አገልግሎት ከመዋሉ በተጨማሪ፣ ለተመራማሪዎች ምቹ ማረፊያ በመሆን በቅርሱ ዙሪያ የሚደረጉ ጥናቶችን እያገዘ ይገኛል።
ሐላላ ኬላ በብሔራዊ ቅርስነት የተመዘገበ ቢሆንም፣ እስካሁን በጥናት በዝርዝር የተለየው ከ83 ኪሎ ሜትር በላይ የሆነው ክፍል ብቻ ነው።
የአካባቢው ማኅበረሰብ ቅርሱ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ይህንን ግብ ለማሳካት ሰፋፊ የመስክ ጥናቶችን የማካሄድ፣ ሰነዶችን የማደራጀት እንዲሁም የግድብ እና የልማት ሥራዎችን ከቅርስ ጥበቃ ጋር አቀናጅቶ የመምራት ሥራ ተጀምሯል።
የድንጋይ ድርደራ ጥበብ እና የዳውሮ ነገሥታት ታሪክ ኢትዮጵያ ጥልቅ ሥልጣኔ፣ የምህንድስና ጥበብ እና ትውልድ ተሻጋሪ ታሪክ እንዳላት ይመሰክራሉ።
የትናንት ወረትን በዛሬ ጠንካራ ሥራ ማስዋብን መሠረት ያደረገው የመደመር መንግሥት ቅርሱን መጠበቅ፣ በጥናት ማስደገፍ እና ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ተግባሩን አጠናክሯል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: