Search

ቀጣናውን ከጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክር ወደ ትብብር እና መረጋጋት መለወጥ ያስፈልጋል

ረቡዕ ኅዳር 16, 2019 52

5ኛው የአፍሪካ ቀንድ የቀይ ባሕር ጂኦ ስትራቴጂያዊ ምኅዳር፣ ጂኦ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር አዳም ተስፋዬ እንደገለፁት፣ የአፍሪካ ቀንድ ውይይት መድረክ ዋና ዓላማ ቀጣናውን ከጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክር ወደ ትብብር እና መረጋጋት መለወጥ የሚቻልበትን መንገድ መቃኘት ያስፈለጋል።

ቀጣናው አሁን ላይ እንደ ግጭት እና የጸጥታ ስጋቶች፣ የተበታተነ የኢኮኖሚ ትብብር እና የእርስ በእርስ አለመተማመን ችግሮችን እያስተናገደ መሆኑን ጠቁመዋል።

እነዚህ ችግሮች የቀጣናውን መልክዓ ምድራዊ ቅርበት እና የጋራ ጥቅሞች ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም እንቅፋት መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ግዛቸው አስራት (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በአፍሪካ ቀንድ የሚታዩ የጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክሮችን እና የተበታተነ ትብብርን ወደ ሰላም፣ መረጋጋትና የጋራ ብልጽግና ለመለወጥ የቀጣናው ሀገራት በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ተናግርዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ቀይ ባሕርን፣ የኤደን ባሕረ ሰላጤን፣ የሕንድ ውቅያኖስን እና ሰፊውን መካከለኛ ምሥራቅ የሚያገናኝ ስትራቴጂያዊ መገኛ ያለው ቀጣና መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በመሠረተ ልማት እና በቀጣናዊ ትሥሥር ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም እንደሚፈጥርለት አመልክተዋል።

የባሕረ ሰላጤ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የዓለም ኃያላን ሀገራት እያደገ የመጣ ተሳትፎ የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባሕርን ጂኦፖለቲካዊ እና ጂኦ-ኢኮኖሚያዊ ምኅዳር እየቀረጸው እንደሚገኝ በአፍሪካ ኅብረት የምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና ጸጥታ ጥናት ዳይሬክተር ፖውል ሳይመን ሀንዲ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

የቀጣናው ሀገራት ሉዓላዊ ጥቅሞቻቸውን እየጠበቁ እና የሚፎካከሩ ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎቶችን እያስተዳደሩ ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን እና የውጭ አጋርነቶቻቸውን ማስተናገድ ይችላሉም ነው ያሉት።

የአፍሪካ ቀንድ የትብብር ሥርዓትን ለመቅረጽ ያለመው 5ኛው የምክክር መድረክ ​ቀጣናውን ከጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክር እና ከተበጣጠሰ ትብብር ወደ የጋራ ባለቤትነት፣ ራስን የመወሰን አቅም እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ መደጋገፍ ለማሸጋገር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በወንድማገኝ ኃይሉ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: