Search

የመሶብ አገልግሎትን በመቀሌ ለማስጀመር ቅድመ-ዝግጅቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል

ረቡዕ ኅዳር 16, 2019 42

በመቀሌ ከተማ የተቀናጀ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችል የማደራጀት እና የአቅም ግንባታ ሥልጠና በአዲስ አበባ እየተሰጠ ይገኛል።

ሥልጠናው እየተሰጠ ያለው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የመሶብ አገልግሎት እና በመቀሌ ከተማ አስተዳደር መካከል የተደረሰውን የጋራ ስምምነት ተከትሎ ነው፡፡

በዚህም በመቀሌ ከተማ የመሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ስምዖን ተስፋማርያም የሚመራው ባለብዙ ዘርፍ ቴክኒካል ቡድን የተግባር ዳሰሳ እና የመስክ ምልከታን ያካተተ ሥልጠና በአዲስ አበባ በሚገኝው የመሶብ አገልግሎት ማዕከል በመውሰድ ላይ ይገኛል።

ሥልጠናው በዋናነት በአራት ቁልፍ ማዕቀፎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ እነርሱም የተቀናጀ፣ ፈጣን እና ተደራሽ የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ መርሆዎችን መረዳትን ያካተተው የመሶብ ፅንሰ-ሐሳብ እና አሠራር እንዲሁም ወደ ማዕከሉ የሚገቡ አገልግሎቶችን በጥራት እና በቅደም ተከተል የመለየትና የማዋቀር ሥራ ናቸው።

በተጨማሪም ዘመናዊ ዲጂታል ሥርዓቶችን በመጠቀም የአገልግሎት ቅልጥፍናን ማሳደግ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ትግበራ እና ለአገልግሎት መስጫው የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል በአግባቡ በማዋቀር የሥራ ድልድል የማዘጋጀት የሰው ሀብት ማደራጀት ተግባራት በሥልጠናው ተካትተዋል።

ከአቅም ግንባታ ሥልጠናው ጎን ለጎን በመቀሌ ከተማ ለመሶብ አገልግሎት መስጫ ማዕከል የሚውል ሕንፃ የማዘጋጀት እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች በትይዩ እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል።

የከተማው አመራር እና ቴክኒካል ቡድን ከሥልጠናውና ከመስክ ምልከታው የሚያገኙትን ተሞክሮ በመቀመር፣ ሀገር አቀፉን የመሶብ አገልግሎት መርሐ-ግብር በመቀሌ ከተማ በተግባር በመምራት ወደ ላቀ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግሩት ተጠቁሟል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: