Search

በቼክ ሪፐብሊክ ለሚገኙ አስጎብኚ ድርጅቶች ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ መድረክ ተካሄደ

ማክሰኞ ነሐሴ 20, 2017 163

ሁለተኛ ቀኑን በያዘው የሉሲ (ድንቅነሽ) እና ሰላም ቅሪተ አካላት ኤግዚቢሽን ጎን ለጎን ለቼክ አስጎብኚ ድርጅቶች ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ መድረክ ተካሂዷል።

በበርሊን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባዘጋጀው በዚህ መድረክ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ/ፕ)፣ በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር እስክንድር ይርጋ፣ የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተሮች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ፍፁም ገዛኸኝ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቼክ ተወካይ ወ/ሮ ማህሌት ከበደ ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት አምባሳደር እስክንድር ይርጋ፤ መድረኩ ኢትዮጵያ በቼክ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን እና ትስስር ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

አስጎብኚ ድርጅቶች ኢትዮጵያን በቱሪዝም መዳረሻ ፓኬጃቸው ውስጥ እንዲያስገቡና እንዲያስተዋውቁም አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተሮች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ፍፁም ገዛኸኝ፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ያሏትን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ሀብቶች አስረድተዋል።

ሀይማኖታዊና ባህላዊ የሆኑ በዓላትንም አስተዋውቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቼክ ተወካይ ወ/ሮ ማህሌት ከበደ በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ የቱሪዝም ዘርፉን እድገት ለማረጋገጥ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በመድረኩ 29 የሚደርሱ አስጎብኚ ድርጅቶች ተሳትፈዋል።

በመቅደላዊት ደረጀ