የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በትግራይ ክልል ከዚህ በኋላ የጦርነት ሳይሆን የልማት ጥያቄ ብቻ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትግርኛ ቋንቋ ያደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስደሰታቸው እና የፌዴራል መንግሥት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት መረዳታቸውን ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግሥት ትግራይን ወደ ተሻለ ሰላም እና ልማት ለማሸጋገር እየሠራ እንደሚገኝ ተረድተናል ነው ያሉት።
"የትግራይ ሕዝብ የልማት እና የሰላም ጥያቄዎቹ ሊፈቱለት ይገባል" ያሉት ነዋሪዎቹ፣ “ያለፈው ጦርነት ያስከተለብን ቀውስ በድጋሚ እንዲፈጠር አንፈልግም” ሲሉ አስምረውበታል።
በትግራይ ክልል የነበረውን ጦርነት በንግግር የፈታው የፕሪቶሪያው ስምምነት የትግራይ ወጣቶች ትከሻቸው መሣሪያ ሳይሆን ሥራን እንዲሸከሙ፣ ተማሪዎችም ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ያስቻለ ነው።
በስምምነቱ መሠረት የፌዴራል መንግሥት በጦርነቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ጠግኗል፤ ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን አዳርሷል፤ ተፈናቃዮችንም የመመለስ ሰፊ ሥራን በመሥራት ላይ ይገኛል።
ሆኖም ህወሓት ከዚህ በተቃራኒ ስምምነቱን በጣሰ መልኩ ለጦርነት ዝግጅት እያደረገ ይገኛል ብለዋል ነዋሪዎቹ።
"ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ማክበር አለበት" ያሉት ነዋሪዎቹ፤ የትግራይ ሕዝብ መሥራት፣ መለወጥ እና ከወንድም ሕዝቦች ጋር የኢትዮጵያ ዋልታ መሆን እንደሚፈልግ አረጋግጠዋል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ
#EBC #Ebcdotstream #Ethiopia #Tigray #peace #PretoriaAgreement