የኢትዮጵያ የጤና ተቋማት ዘመናዊ አሰራሮችንና የፈጠራ ስልቶችን በመተግበር የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራታቸውን ሊያሻሽሉ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ አሳሰቡ።
ይህ ጥሪ የቀረበው በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተካሄደው የ4ኛው ዙር የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው።
በዕለቱም የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ 30 ሆስፒታሎች የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፣ የሆስፒታሎች ጥምረት ተቋማትን እውቅና ከመስጠት ባለፈ፣ በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን ትልቅ ፋይዳ አለው።
በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጤናው መሠረተ ልማት ላይ የተመዘገቡ ስኬቶች የሚበረታቱ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት በሀገሪቱ የነበሩት የኦክሲጅን ማምረቻዎች 3 ብቻ የነበሩ ሲሆን፣ ዛሬ ላይ ወደ 64 ማደጋቸው የዘርፉን ጥንካሬ ያሳያል ብለዋል።
በተጨማሪም ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የሕክምና ግብዓቶች ለክልሎች መሰራጨታቸውና የግል ጤና ተቋማት ቁጥር በሦስት እጥፍ ማደጉ የጤና አገልግሎት ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ እየተከናወነ ያለው ሥራ ውጤት ነው።
መንግሥት የጤና አገልግሎትን ጥራት፣ ፍትሐዊነትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር መቅደስ፣ ሆስፒታሎች ትስስራቸውን በማጠናከር ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ አሳስበዋል።
በሳምሶን ገድሉ