Search

የኢትዮጵያ ሠራዊት ሙዚየም የጀግንነት ታሪካችን ሕያው ምስክር ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ዓርብ የካቲት 27, 2018 76

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በጃንሜዳ አካባቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሠራዊት ሙዚየም ጎብኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት፤ ሙዚየሙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያለፈበትን የዘመናት የጀግንነት ጉዞ የሚመሰክሩ ሕያው አሻራዎች የታቀፉበት ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።

1950ዎቹ ጀምሮ እንዲቋቋም ሲታለም የቆየው ይህ የጦር ሙዚየም፣ በለውጡ መንግሥት ቁርጠኝነት ተቋማዊ ቁመና ተላብሶ እውን መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ይህም ስኬት ወደፊት ለሚገነባው ግዙፍ ብሔራዊ የሠራዊት ሙዚየም እንደ ማዕዘን ድንጋይ የሚወሰድ መሆኑን አብራርተዋል።

በሙዚየሙ ውስጥ ከዓድዋ ዘመን በፊት የነበሩ ብርቅዬ መሣሪያዎች፣ የነገሥታት ትጥቆች፣ እንዲሁም 1900 ጀምሮ ያለውን ዘመናዊ የተቋም ግንባታና የጦር መሣሪያዎች ዝግመተ ለውጥ የሚያሳዩ ታሪካዊ ቅርሶች እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

ሙዚየሙ ለሠራዊቱና ለትውልድ ታሪክንና ዕውቀትን የሚያስታጥቅ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አፍሪካውያንና መላው በፀረ ቅኝ አገዛዝ የታገለ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ይሄንን ሙዝየም በመመልከት የራሱን ታሪክ እንዲያደንቅ እጋብዛለሁ ብለዋል።

መንግሥት የሠራዊቱ ገድል ለትውልድ እንዲሸጋገር በዘመናዊ መንገድ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል።

#EBC #Ethiopia #DefenseMuseum #MilitaryHistory #TemesgenTiruneh #NationalDefense