Search

በዋንጫ የተንቆጠቆጠው የነጩ ቤት 124 ዓመታት ጉዞ

ቅዳሜ የካቲት 28, 2018 42

በዓለማችን የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ በስኬት ማማ ላይ የሚገኘው እና የክለቦች ቁንጮ ተብሎ የሚጠራው ሪያል ማድሪድ 124ኛ የምሥረታ ዓመቱን አክብሯል።

በ1902 በስፔን መዲና ማድሪድ የተመሠረተው ይህ ታሪካዊ ክለብ በሜዳ ላይ ከሚያሳየው ድንቅ ብቃት ባሻገር በጠንካራ የክለብ አስተዳደሩም አርአያነት ያለው ተቋም ለመሆን በቅቷል። 

ክለቡ ሲመሠረት "ማድሪድ እግር ኳስ ክለብ" የሚል ስያሜ የነበረው ሲሆን እስከ 1920 ድረስም በዚህ መጠሪያው በስፔን የተለያዩ ውድድሮች ላይ ሲሳተፍ ቆይቷል።

ሆኖም በ1920 ከስፔን ንጉሣውያን ቤተሰቦች በተሰጠ ትዕዛዝ "ሪያል" (ንጉሣዊ) የሚል የክብር ስያሜን ከፊቱ በማስቀደም የአሁኑን "ሪያል ማድሪድ" የሚለውን መጠሪያ ሊይዝ ችሏል።

ከክለቡ አስደናቂ የስኬት ጉዞዎች 1950ዎቹ ወርቃማ ዘመኑ ሊባል የሚችል ነበር። በወቅቱ እንደ አልፌርዶ ዲ ስቲቫኖ እና ፈረንች ፑሽካሽ ባሉ ድንቅ ኮከቦች የታጀበው ቡድኑ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ከ1956 እስከ 1960 በተከታታይ አምስት ጊዜ በማንሳት በታሪክ የማይረሳ አሻራውን አሳርፏል።

ይህ የድል ጉዞ ቀጥሎም ክለቡ እስካሁን 15 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን፣ 36 ጊዜ የላሊጋን፣ 20 ጊዜ የኮፓ ዴላሪ እና 13 የስፔን ሱፐር ካፕ ዋንጫዎችን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ድሎችን እንዲያሳካ አስችሎታል። 

ለዚህ ሁሉ ውጤት ከጁሊያን ፓላሲዮስ እስከ ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ያሉ መሪዎች ሚና ላቅ ያለ ነበር። በተለይም ከ1943 እስከ 1978 ክለቡን የመሩት እና ስታድየሙ በስማቸው የተሰየመው ሳንቲያጎ ቤርናቢዩ ቡድኑ በአውሮፓ ኃያል እንዲሆን መሠረት ጥለዋል። 

የአሁኑ ፕሬዚዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ደግሞ "ጋላክቲኮ" በሚለው ፖሊሲያቸው የዓለምን ምርጥ ተጫዋቾች ወደ ነጩ ቤት በማምጣት ክለቡን በፋይናንስ ረገድ የዓለማችን ባለጸጋ ቡድን ማድረግ ችለዋል።

በዚህ ዝነኛ ክለብ ውስጥ እንደ አልፌርዶ ዲህ ስቲቫኖ፣ ራዑል ጎንዛሌዝ፣ ዚነዲን ዚዳን፣ ሮናልዶ ናዛሪዮ፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ዴቪድ ቤካም፣ ሉካ ሞድሪች እና ካሪም ቤንዜማ ያሉ እግር ኳስን የለወጡ ደማቅ ከዋክብት ተጫውተው በማለፋቸው ሪያል ማድሪድ ሁልጊዜም በክዋክብት የተሞላ ታሪካዊ ቤት ሆኖ ይኖራል።

በሀብተሚካኤል ክፍሉ

#EBC #Ebcsport #RealMadrid #124Years #FootballHistory