የመራጮች ምዝገባ መጀመር በሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ከሆነው የምርጫ ምዕራፍ አንዱ ነው።
ይህ ሂደት ዜጎች ዴሞክራሲያዊ ልምምድ እንዲጎለብቱ የሚያግዝ፣ በምርጫ ብቻ መንግሥት የማዋቀር ቁርጠኛ አቋማቸውን በተግባር የሚያሳዩበት ሲሆን ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ እና ተቋማዊ አሠራርን እንዲያጠናክሩ ዕድል የሚፈጥር የሲቪክ ተግባር ነው።
ሕገ-መንግሥታዊ መብትን በተግባር
በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት የተደነገገው የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ወደ ተግባር የሚቀየረው በመራጮች ምዝገባ ሂደት ነው።
መመዝገብ አንድ ዜጋ በሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ በሕጋዊ መንገድ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ቅድመ ሁኔታ ማሟላት ማለት ሲሆን፣ ይህም የግል መብትን ከመጠቀም ባለፈ ለሕግ የበላይነት መከበር የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ልምምድን ማጠናከር
ዴሞክራሲን ሕዝባዊ እና ተቋማዊ ባህል ማድረግ ለዳበረ ዴሞክራሲ ወሳኝ ምዕራፍ ነው። ስለሆነም ዴሞክራሲን በተግባር ከመለማመድ እና ተከታታይነት ያለው የምርጫ ባህልን ከመገንባት አንፃር የምዝገባ ሂደት ትልቅ ሚና አለው። ዜጎች በምዝገባ ወቅት የሚያሳዩት ተሳትፎ፦
* በምርጫ ተቋማት እና አሠራሮች ላይ እምነት እንዲገነባ ያደርጋል፤
* ተከታታይነት ያለው እና ሥርዓቱ የሚታወቅ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲሰፍን ይረዳል፤
* ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዳበረ የሚሄድ የዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ልምድ እንዲዳብር መሠረት ይጥላል።
የሠለጠነ የፖለቲካ ተሳትፎ ባህል ያዳብራል
የመራጮች ምዝገባ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እና የሠለጠነ የፖለቲካ ባህል እንዲጎለብት ያደርጋል።
ይህም ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በተቋማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ያለውን ፋይዳ የጎላ ያደርገዋል።
የባለቤትነት ስሜት
ምዝገባው ዜጎች በሂደቱ ላይ ያላቸውን የባለቤትነት ስሜት የሚያሳድግ ነው። ይህ ደግሞ ለሀገራዊ መረጋጋት እና ለተቋማዊ ዕድገት ወሳኝ ነው።
ስለሆነም የመራጮች ምዝገባ በኢትዮጵያ ለሚገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደ መነሻ ተግባራዊ ልምምድ የሚወሰድ ተግባር ነው።
ዕድሜዎ 18 እና ከዚያ በላይ ከሆነ፣ በተቀመጡት የመራጭነት ምዝገባ አማራጮች (በምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት፤ "ምርጫዬ" የሞባይል መተግበሪያን በመጠቀም እንዲሁም) በምርጫ ቦርድ ድረ-ገጽ (Online) አማካኝነት ምዝገባዎን በማከናወን የድርሻዎን ይወጡ ሲል ምርጫ ቦርድ ጥሪ አቅርቧል።
#EBC #Ethiopia #elections #7thgeneralelection #NEBE