Search

የሿሿ ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ 5 ተጠርጣሪዎች ተያዙ

ማክሰኞ ነሐሴ 20, 2017 236

በአዲስ አበባ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ የማታለል (የሿሿ) ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ከነ ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ገለፁ፡፡

ኮማደር ማርቆስ እንደገለፁት የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የፒያሳ ፖሊስ ጣቢያ ነሐሴ 16 ቀን 2017 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዓት ሄነሪኮ ኬክ ቤት አካባቢ በተሽከርካሪዎች ላይ ድንገተኛ ፍተሻ በሚያደርግበት ወቅት የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 1 አ/አ 11631 ሚኒባስ ታክሲ ከፍተሻው ለመዳን መንገድ በመቀየስ ወደመጣበት አቅጣጫ ይመለሳል፡፡

ፖሊስም በመጠራጠር ተሽከርካሪውን ተከታትሎ በመያዝ ባደረገው ፍተሻ ከተለያዩ ግለሰቦች የተሰረቁ 4 የሞባይል ቀፎዎችን ከ5 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋል ችሏል ብለዋል ኮማንደሩ፡፡

ፖሊስ ከተጠርጣሪዎቹ እጅ ላይ በተገኙ ስልኮች ላይ ባደረገው ማጣራት የተሰረቁ ስለመሆናቸው ከግል ተበዳዮች ማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን፤ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በእነዚህ ግለሰቦችና ተሽከርካሪ ወንጀል የተፈፀመበት ግለሰብ ካለም ፒያሳ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ማመልከት እንደሚችል አክለዋል፡፡

ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን ወንጀል ፈጽሞ ከፖሊስ ዓይን ማምለጥ የማይችል መሆኑን ተገንዝቦ ከመሰል ድርጊት ራሱን ማራቅ እንደሚኖርበትም ኮማደር ማርቆስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በላሉ ኢታላ

#ebc #ebcdotstream #police #aapolice