በደቡባዊ ምእራብ በምትገኘው የኮሎምቢያ ከተማ ካውቻ እ.አ.አ በ1981 የተወለዱት ፍራንሲያ ማርክኬዝ ህይወትን ለማሸነፍ የቤት ሰራተኝነትን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎችን ሰርተዋል።
በዚህ አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ የወጣትነት ህይወታቸውን ያሳለፉት ፍራንሲያ፤ የኑሮ ውጣ ውረድ ከትምህርታቸው ሳያሰናክላቸው የህግ ትምህርት ተምረው የማህበረሰቡን መብቶች ለማስከበር ግንባር ቀደም ተሟጋችም ነበሩ።
እ.አ.አ በህዳር 17 2014 ላቶማ በምትባለው የኮሎምቢያ ትንሽ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የአቪጃስ ወንዝን ከብክለት ለመታደግ የተዘጋጀ 560 ኪሎሜትር የሚሸፍን ሰልፍ ተደርጎ ነበር።
በወቅቱ የ32 ዓመት እድሜ የነበራቸውና አሁን ላይ የመጀመሪያዋ የኮሎምቢያ ጥቁር ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ፍራንሲያ ማርክኬዝ ሰልፉን በመሪነት አዘጋጅተው ነበር፡፡
ይህ ብዙ ከተሞችን አቋርጦ የሚጓዝ ረጅም ሰልፍ መነሻውን ላቶማ አድርጎ እስከ ርእሰ ከተማዋ ቦጎታ ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን አላማውም የኮሎምቢያ መንግስት ወንዙን ከብክለት እንዲታደግ ለማሳሰብ ነበር።
በዚህም መሰረት በህዳር 17 2014 ሰማንያ የሚሆኑ የአካባቢው ሴቶች የተካተቱበት የሰላማዊ ሰልፍ ቡድን ምግብ፣ ውሀ እና ለመኝታ የሚጠቀሙበትን ልብስ አዘጋጅተው በፍራንሲያ ማርክኬዝ መሪነት የ560 ኪ.ሜ የሚረዝመውን መንገድ ጀመሩ።
በፍራንሲያ የሚመሩት ሰማንያ የላቶማ ከተማ ነዋሪዎች እጅግ ፈታኝ የሆነውን መንገድ እየዘመሩ በየደረሱበት ከተማ ጥያቄያቸውን እያሰሙ በቀን ከ50 ኪ.ሜ በላይ በመጓዝ ከአስር ቀናት በኋላ ዋና ከተማዋ ቦጎታ ሲደርሱ ጉዟቸውን ከጀመሩበት እለት አንስቶ መረጃው የነበራቸው የዋና ከተማዋ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል አደረጉላቸው።
የላቶማ ከተማ ነዋሪዎች ህይወታቸው የተመሰረተው በአቪጃስ ወንዝ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ወንዝ አሳ ያጠምዳሉ፤ ለመስኖ አገልግሎት ያውሉታል፤ እንዲሁም ለመጠጥና ለአጠቃላይ የውሀ ፍላጎታቸው ይገለገሉበታል።
ሆኖም በአካባቢው በህገ-ወጥ መንገድ የወርቅ ማእድን የሚያወጡ ኩባንያዎች ወርቁን ለማጣራት በሚጠቀሙባቸው ኬሚካሎች ምክንያት በአቪጃስ ወንዝ ላይ ብክለት እየደረሰ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ማስተዋል ጀመሩ፡፡
በውሃ ብክለቱ የተነሳ አሳዎች መሞታቸውንና ወንዙም መመረዝ መጀመሩን ያስተዋሉት የትንሿ ከተማ ነዋሪዎች፤ ይህንን ተቃውመው ወንዙን ከብክለት ለመታደግ ተቃውሞ ጀመሩ።
በዚህ የተቃውሞ ሂደት ላይ ፍራንሲያ ማርክኬዝ ዋነኛ ሰው የነበሩ ሲሆን፤ ወደ ፖለቲካው ዓለም የተቀላቀሉትም በዚሁ መንገድ ነው።
በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ፍራንሲያ ማርክኬዝ፤ በህገ-ወጥ ማዕድን አውጪዎች በአቪጃስ ወንዝ ላይ እየደረሰ ያለውን ብክለት ለመንግስት አካላት አስረዱ።
ከዚህ በኋላም መንግስት በፍራንሲያና አጋሮቿ ጥረት በአካባቢው ያለውን የወንዝ ብክለት ሁኔታ ማጤን በመጀመሩ ብዙም ሳይቆይ ድካማቸው ፍሬ አፍርቶ ወንዞችን ከብክለት የሚታደግ ህግ ከማውጣቱም በላይ ወንዙን ለብክለት የዳረጉትን ህገ-ወጥ ማእድን አውጭዎች በኃይል ከቦታው ማስለቀቅ ችሏል፡፡
በህገወጥ ማዕድን አውጭዎች ላይ በመንግስት ከተወሰደው ከዚህ እርምጃ በኋላ፤ የፍራንሲያ ህይወት አደጋ ላይ በመውደቁ የተወለዱበትን አካባቢ በመልቀቅ ኑሯቸውን በዋና ከተማዋ ቦጎታ ለማድረግ ተገደዱ።
ፍራንሲያ ማርክኬዝ በዚህ ጥረታቸውም ከተለያዩ የአካባቢ ተሟጋች ቡድኖች እውቅናና ሽልማት አገኝተዋል።
በዚህ የሰብዓዊ መብት ትግል የተጀመረው የፍራንሲያ የህይወት ጉዞ ቀጥሎ ወደ ፖለቲካው አለም አምርቶ፤ በ2021 የመጀመሪያዋ ጥቁር የኮሎምቢያ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ተመርጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለትም ከኮሎምቢያ ምክትል ፕሬዝዳንት ፍራንሲያ ማርክኬዝ ጋር በተለያዩ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
በዋሲሁን ተስፋዬ