Search

መስፈርቶችን የማያሟሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከትምህርት ሥርዓቱ እንዲወጡ ይደረጋል፡- የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን

ማክሰኞ ነሐሴ 20, 2017 184

የኢትዮጵያ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን በአዲስ አበባ በሚገኙ የግል ከፍተኛ የትምህር ተቋማት የብቃት ምዘና አካሂዶ ውጤቱን ይፋ አድርጓል፡፡

በከተማዋ ከሚገኙ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል የ3 ተቋማት 3 ካምፓሶችና 17 ፕሮግራሞች የብቃት ምዘና ዝቅተኛውን መስፈርቶችን በማሟላታቸው ፍቃደቸው ለአንድ ዓመት እንዲፀናላቸው ተደርጓል፡፡

በትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የተቋማት ፈቃድ አሰጣጥ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ህይወት አሰፋ እንደሚሉት በከተማዋ በግል ከፍተኛ ተቋማት በተሰራው የብቃት ምዘና 25 ተቋማት፣ 37 ካምፓሶች እና 146 ፕሮግራሞች በ12 ወራት ውስጥ ዝቅኛውን መስፈርት እንዲያሟሉ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል፡፡

62 ተቋማት ስር የሚገኙ 66 ካምፓሶች እና 256 ፕሮግራሞች ደግሞ ዝቅተኛውን የብቃት ምዘናው ባለማሟላታቸው በ6 ወራት ውስጥ መስፈርቱን እንዲያሟሉ ጊዜ የተሰጣቸው ናቸው ብለዋል፡፡

ተቋማቱ በተሰጠው ጊዜ ዝቅተኛ የምዘና መስፈርቶችን የማያሟሉ ከሆነ ከትምህርት ሥርዓቱ እንዲወጡ እንደሚደረግም መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሮ ህይወት አሰፋ ገልፀዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ያካሄደው የዳግም ምዝገባ ስርዓት ወጥነት ያለው የአሰራር ስርዓት ለመፍጠር፤ አሁናዊ የተሟላ መረጃ እንዲኖር እንዲሁም፤ በግልና በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ያለው የፍቃድ አሰራር ልዩነትን ለማስቀረት ይረዳል ብለዋል መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ፡፡

በተቋማቱ ህጋዊ የአሰራር ስርዓት ለማስፈን፤ ተዛማጅ ካሆልኑ የንግድ ስራዎች ጋር በመቀላቀል ለትምህርት ምቹ ባልሆኑ አካባቢዎች የሚሰጠውን የማስተማር ስራ በማስቀረት ተቋማት በራሳቸው ወይም ሙሉ ህንፃ ተከራይተው እንዲሰሩ እንደሚያችልም አንስተዋል፡፡

በተለይም ተቋማት የማስተማሪያ ህንፃ መገንባት ወይም መከራየት እንዲሁም መምህራን ማሟላት ግዴታ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ተቋማቱ ሰነዶቻቸውን፣ አደረጃጀታቸውን፣ መዋቅሮቻቸውን በአዲሱ የጥራት መስፈርት መሰረት እንዲከልሱ በማድረግ የተረጋገጠ ትምህርት ማስረጃ አሰጣጥን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚስችልም መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሮ ህይወት አሰፋ ገልፀዋል፡፡

የዘርፉን ዝቅተኛ መስፈርት በማሟላት ማህበረሰቡ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኝ እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት፡፡

የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ መስፈርቶችን ከ6 እስከ 1 ዓመት ውስጥ ማሟላት ካልቻሉ ከትምህርተ ስርዓቱ እንዲወጡ እንደሚደረግም መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሮ ህይወት አሰፋ አስታውቀዋል፡፡

በላሉ ኢታላ

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #Education