የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ትውልዱ የዘመናት የልማት ቁጭቱን በራሱ አቅም ታላቁ የሕዳሴ ግድብን እውን በማድረግ መወጣት መቻሉን ገለፁ።
ኢትዮጵያ በዜጎቿ ርብርብ ያሳካችውን ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ግድብ በቅርቡ በልዩ ድምቀት ለመመረቅ በዝግጅት ላይ መሆኗን ጠቅሰዋል።
የሕዳሴ ግድብ የሚያመነጨው ኤሌክትሪክ ሀገራዊና ቀጣናዊ የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት ትልቅ አቅም እንደሆነም ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በውሃ ሃብቶቿ ለመጠቀም በተለያዩ ጊዜያት ሙከራዎችን ስታደርግ እንደነበር አንስተው፤ ሕዳሴ ግድብ የቁጭት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድ ሕዳሴ ግድብን በብርቱ ክንዱ እውን በማድረግ የኢትዮጵያን የዘመናት ቁጭት ያሳካ ጀግና ትውልድ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ግዙፉ ፕሮጀክትም ለቀጣዩ ትውልድ ጭምር የይቻላል መንፈስን የሚያወርስ ደማቅ የልማት አሻራ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
በሀገር ውስጥ እና በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደት ያለአንዳች ልዩነት በንቃት በመሳተፍ ደማቅ ታሪክ መፃፋቸውንም አውስተዋል።
ፕሮጀክቱ ለዘመናት የቆየውን ኢ-ፍትሐዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀም የቀየረ መሆኑንም አንስተዋል።
ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በቂ ውሃ በመልቀቅ የጎርፍ አደጋን ማስቀረት እንዳስቻለም ገልፀዋል።
በግዙፉ ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ዜጎች ከትውልድ ትውልድ ሲዘከሩ ይኖራሉ ብለዋል።
#EBCdotstream #Ethiopia #GERD #Megaproject