ፕሮጀክት ጀምሮ ያለመጨረስ መለያዋ የነበረው ኢትዮጵያ በፕሮጀክት አፈፃፀም ትልቅ ለውጥ ልታስመዘግብ ችላለች ሲሉ በከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የመሠረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት ገለፁ።
ከአስተሳሰብ ጀምሮ እስከ አሠራር የዘለቁ ሪፎርሞች በሜጋ ደረጃ ያሉ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ተሠርተው እንዲጠናቀቁ ማስቻላቸውን አቶ የትምጌታ ለኤፍ.ኤም አዲስ 97.1 ገልፀዋል።
በዚህም ፕሮጀክቶችን ጀምሮ መጨረስ ብቻ ሳይሆን ተጓትተው እና ተቋርጠው የነበሩትም እንዲጠናቀቁ ማድረግ መቻሉንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት።

የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፥ ፈጠራ እና ፍጥነት በታከለበት መልኩ ትኩረት ሰጥተን ከሰራን አንድ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የልማት ዘርፍ ማደግ ይችላል ሲሉ ገልፀዋል።
እንዲህ ያለው አሠራር ተጨባጭ ለውጥ የሚያላብስ መሆኑን ገልፀው፤ በዕቅድ ተይዘው በአመርቂ አፈፃፀም የተጠናቀቁ የከተማዋ ፕሮጀክትን በአብነት ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም ፕሮጀክት ስናቅድ በችኮላ ተጀምረው የሚገቱ ሳይሆን በብርቱ የሥራ ባህል የሚጠናቀቁ እንዲሆኑ ነው ሲሉ አክለዋል።
በአፎሚያ ክበበው
#EBCdotstream #Urbanization #Reform #ProjectDelivery