ሕገ-ወጥ ስደተኞች ከሀገር ለመውጣት በሚያደርጉት ጥረት ሁሉንም የመውጫ በሮች ይጠቀማሉ።
በዚህ ሙከራቸው ታዲያ ብዙውን ጊዜ በአየርም ሆነ በየብስ ኬላዎች በፌዴራል እና በክልል የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ይውላሉ።
ሆኖም ዜጎች የሕገ-ወጥ ስደትን አስከፊ ገጽታዎች ባለመረዳት በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ቀቢፀ ተስፋ ተነሣሥተው በባህር ውኃ የሚበሉበት፣ በወጡበት በረሃ የሚቀሩበት አጋጣሚ ብዙ ነው።

በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ፍልሰት ትብብር ጥምረት ሴክሬታሬት ኃላፊ አብረሃም አያሌው ከኢቢሲ የአዲስ ቀን መሰናዶ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ መግቢያ እና መውጫ በሮችን በመቆጣጠር ሕገ-ወጥ ስደትን ማስቀረት አይቻልም።
ችግሩን ለመቅረፍ ገፊ ምክንያቶችን በመለየት በቀጣይነት መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው የሚናገሩት።
የሕገ-ወጥ ፍልሰትን አስከፊ ገጽታዎች እና የሚያስከፍለውን መሥዋዕትነት በተመለከተ ለዜጎች ግንዛቤ መፍጠር፣ በሀገር ውስጥ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ሕጋዊ የሥራ ስምሪትን ማጠናከር፣ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ችግር ተደራሽ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ኃላፊው አብራርተዋል።
በአጠቃላይ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም ሁሉን አቀፍ ሥራዎችን ማከናወን አስፈላጊ እንደሆነ ነው የገለጹት።
የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች የሚሰማሩት ስደት ላይ ብቻ ሳይሆን ኮንትሮባንድ፣ ሽብርተኝነት፣ የመሣሪያ እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ወንጀሎች ላይ ተሳትፎ እንደሚያደርጉም አቶ አብረሃም አያሌው ተናግረዋል።

በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኤርሚያስ ተክሌ በበኩላቸው፣ በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ጠቁመዋል።
በሕጋዊ መንገድ የሥራ ስምሪት ለሚያደርጉት ዜጎች ያለ ደላላ ጣልቃ ገብነት በሕጋዊ ኤጄንሲዎች የሚሰማሩበት ዘመናዊ አሠራር መዘርጋቱንም ተናግረዋል።
የሥራ ስምሪት ክትትል እና ቁጥጥር ለማድረግ እንዲያስችል በሕግ፣ በቴክኖሎጂ እና በአሠራር ሥራዓት የተደገፈ ለማድረግ የተዘረጋው መዋቅር ዘመናዊ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት የሚያደርጉ ዜጎች ያለ እንግልት ጉዳያቸውን እንዲጨርሱ ለማስቻል የጤና ምርመራ፣ የሙያ ሥልጠና፣ የፓስፖርት አገልግሎት ሰጪ ማዕከላትን ቁጥር የማስፋት ሥራ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
በመሐመድ ፊጣሞ
#EBC #ebcdotstream #illegalmigration #refugees