ኢትዮጵያ አፍሪካ አህጉር አቀፍ ሚዲያ እንዲኖራት እያከናወነች ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቃለች።
ኢትዮጵያ ይህን ያለችው ዛሬ በተከፈተው የምሥራቅ አፍሪካ የኮሙኒኬሽን ማኅበር 15ኛ ጉባዔ ላይ ነው።
15ኛው የምሥራቅ አፋሪካ ኮሙኒኬሽን አሶሴሽን ዓመታዊ ኮንፍረንስ “ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ለአፍሪካ ትሥሥር” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባዔው ንግግር ያደረጉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ አፍሪካ አቋሟን የምታሳውቅበት እና ማንነቷን ለተቀረው ዓለም የምታሳይበት የሯሷ ሚዲያ እንዲኖራት እያከናወነች ያለውን ተግባር አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም አህጉር አቀፉ ሚዲያ ስለአፍሪካ ትክክለኛ መረጃ ከማድረስ ባሻገር የጋራ ሐሳባችንን ለማንፀባረቅ ይጠቅማል ሲሉ ገልጸዋል።
የተዋሀደች እና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የተግባቦት ሥራው የወል ትርክት መገንባት፣ ትምምን ማጠናከር፣ በሀገራት እና ሕዝቦች መካከል ጠንካራ የፖለቲካል-ኢኮኖሚ እና የባህል ውህደት መፍጠር ላይ መሥራት ይገባዋል” ነው ያሉት።
አህጉራዊ እና ቀጣናዊ ውህደትን እውን ማድረግ የመሠረተ ልማት ትሥሥር፣ የተጠናከረ ቀጣናዊ መስተጋብር መኖር፣ የእርስ በርስ ትምምነት መፈጠር፣ የባህል ልውውጥ መጠናከር አስፈላጊ መሆናቸውንም በንግግራቸው አመላክተዋል።
“አስተሳሳሪ የወል ትርክት መገንባት፣ የጋራ ዕድል እና ዕጣ ፋንታ እንዳለን ማስገንዘብ፣ የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የወል ተስፋዎችን እና ፈተናዎችን ማሳወቅ ከአህጉሩ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ይጠበቃል” ነው ያሉት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት ዲን አብዱላዚዝ ዲኖ (ዶ/ር)፣ የማኅበራዊ ሚዲያው የሐሰት መረጃን በማሰራጨት እያስከተለ ያለውን አደጋ ከመከላከል አንፃር ጉባዔው ይመክራል ብለዋል።
የጉባዔው ተሳታፊዎችም ጉባዔው በአህጉሪቱ ውስጥ ያሉ ሀገራትን ለማቀራረብ እና የጋራ ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ ወሳኝ መሆናቸውን ለኢቲቪ ገልጸዋል።
በጉባዔው ከ20 ሀገራት የተወጣጡ 300 የሚጠጉ ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በሳምሶን በላይ
#ebcdotstream #EBC #FDRE_GCS #media