Search

በፈጥኖ ደራሽ ኃይል የታጀበው የሉሲ እና ሰላም የፕራግ ጉዞ

ረቡዕ ነሐሴ 21, 2017 236

የሉሲ እና የሰላም ቅሪተ አካላት ለተወሰነ ጊዜ ቆይታ አውሮፓ ናቸው።

የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት ለማሳወቅ እና ቱሪዝምን ለማጠናከር ታስቦ ለተዘጋጀውን ልዩ ኤግዚቢሽን ምክንያት ወደ ቼክ ሪፐብሊክ የተጓጓዙት ቅሪተ አካላቱ በሀገሪቷ ዋና ፕራግ ከተማ በደረሱበት ወቅት ደማቅ አቀባበል ተደርጓል።

በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ልዩ በረራ የተጓጓዘው የሁለቱ ቅርሶች ቅሪተ አካል ቫክላቭ ሃቭል ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ለሁለት ወራት ወደሚቆይበት የሀገሪቱ ብሔራዊ ሙዚየም እስከሚደስ ለመተኪያ አልባ ቅርሶች የሚገባ ልዩ የእጀባ እና ጥበቃ እንደተደረገ ታውቋል።

ራዲዮ ፕራግ ይህን በተመለከተ እንደዘገበው የሉሲ እና የሰላም ቅሪተ አካላት “URNA” የሚል ስያሜ ባለው የቼክ ሪፐብሊክ የልዩ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጥብቅ የፀጥታ ጥበቃ እየተደረገለት ፕራግ ወደሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም ሰሞኑን ደርሰዋል።


 

የሉሲና ሰላም ቅሪተ አካሎች በማዕከላዊ አውሮፓ ቼክ ሪፐብሊክ በፕራግ ከተማ በሚገኘው ግዙፍ ሙዚየም እየተጎበኙ ይገኛል።

አንድ መቶ አባላት ብቻ ያሉት የሀገሪቷ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ታዲያ ከፍተኛ ለሆኑ ጉዳዮች ብቻ የሚሰማራ እና ከሀገር ውጭም የልዩ ኃይሉ ድጋፍ ሲፈለግ ተንቀሳቅሶ ግዳጁን የሚወጣ መሆኑ ታውቋል።


 

በአፍጋኒስታን እና ኢራቅ አለመረጋጋት በተከሰተበት ወቅት ወደስፍራው በማምራት የቼክ ሪፐብሊክ ኤምባሲን ከጥቃት ለመከላከል ተልኮም ነበር።

ፕራግ ከዓለም እጅግ ሰላማዊ እና አስተማማኝ የፀጥታ ጥበቃ ካላቸው ከተሞች አንዷ ብትሆንም፤ ይህ ጥብቅ የፀጥታ ጥበቃ የቼክ ሪፐብሊክ መንግስት ለምትክ አልባ ቅርሶች ያለውን ትልቅ ቦታ እና ክብር የሚያሳይ ነው ተብሏል።

 

በዋሲሁን ተስፋዬ