የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ከፓኪስታን አየር ኃይል ዋና አዛዥ ኤር ቺፍ ማርሻል ዛሂር አህመድ ባበር ሲዱ ጋር በኢስላም አባድ በሚገኘው የአየር ኃይል ዋና መስሪያ ቤት ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በውይይቱ በሁለቱ ሀገራት አየር ኃይሎች መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር የበለጠ ለማሳደግ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ በኢስላም አባድ የሚገኘው የፓኪስታን አየር ኃይል ዋና መሥሪያ ቤት ቤቱ ሲደርሱ በፓኪስታን አየር ኃይል የክብር ዘብ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በውይይቱ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ ላይ እንደምትገኝ፤ ይህ ለውጥ በኢኮኖሚና በፖለቲካው መስክ ብቻ ሳይወሰን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን በዘመናዊ መልክ ለማዋቀር ስልታዊ ትኩረት እንደተሰጠውም አስረድተዋል።
አዛዡ አክለውም የዘመናዊነት ስራው በሶስት ዋና ዋና ምሶሶዎች ላይ የተገነባ መሆኑን ገልጸው፤ እነርሱም ጠንካራ የሰው ኃይል ልማት፣ የዘመኑን የመጨረሻ ደረጃ ቴክኖሎጂ መታጠቅ እና ወቅታዊ የደህንነት ተግዳሮቶችን ለመቋቋም የሚያስችል አዲስ የሠራዊት አደረጃጀት መፍጠር ናቸው ብለዋል።
በውይይቱ ላይ በዋናነት ከተነሱት ጉዳዮች መካከል በመጪው ወር ስለሚመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነበር።
ሌተናል ጄኔራል ይልማ እንዳብራሩት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ታሪካዊ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክት ከመሆኑ ባሻገር ኢትዮጵያ ለቀጠናው ብልጽግናና መረጋጋት ያላትን ራዕይ መሰረት ነው።
የህዳሴው ግድብ የላቀ ብሔራዊ ኩራታችንና ለተሻለ ነገ ያለንን ቁርጠኝነት የምናሳይበት ማሳያ ነው ያሉት አዛዡ፤ የሀገራችንን የኃይል ፍላጎት ከማሟላቱም ባሻገር ለአፍሪካ ቀንድ የቀጠናው ውህደት፣ ሰላምና የጋራ ደህንነት ግቦች እንደ ማነቃቂያ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
አክለውም የፓኪስታን አየር ኃይል ያለውን ጠንካራ የተግባር ዝግጁነት፣ እያደገ የመጣውን ሁለገብ ዘርፍ ችሎታዎች እና አስተማማኝ የመከላከል አቋሙን አድንቀዋል።
የፓኪስታን አየር ኃይል ዋና አዛዥ ኤር ቺፍ ማርሻል ዛሂር አህመድ፤ አቻቸውን እንኳን ደህና መጡ በማለት ጉብኝቱ በሁለቱ አገራት መካከል እያደገ የመጣውን ግንኙነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
በጋራ የስልጠና መርሃ ግብሮች አማካኝነት በሁለቱ አየር ኃይሎች መካከል ያለውን ወታደራዊ አጋርነት ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ወንድማዊ ግንኙነት ከፍተኛ ዋጋ እንደምትሰጥ በመግለጽ የፓኪስታን አየር ኃይል በአቅም ግንባታ፣ በላቀ ስልጠና እና በክንውን ዘርፎች ለኢትዮጵያ አየር ኃይል ሙያዊ ጥረቶች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ጽኑ አቋም እንዳለው ገልፀዋል።
የአየር ኃይል ዋና አዛዡ የኢትዮጵያን ከፍተኛ የለውጥ ፕሮግራሞች በማድነቅ ፓኪስታን ያላትን ልምድና እውቀት ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
አክለውም ከጋራ ወታደራዊ ልምምዶች እስከ ቴክኒክ ድጋፍ ድረስ በተጨባጭ የትብብር መስኮች ላይ በጋራ ለመስራት ያላቀቸውን ዝግጁነት ገልፀዋል።
ይህንን ጠቃሚ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ይህ ጉብኝት ኢትዮጵያ እያሰፋችው ያለውን የዲፕሎማሲ ተደራሽነትና ፓኪስታን ከቁልፍ የአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን እንዲሁም በሁለቱ ወዳጅ አገራት አየር ኃይሎች መካከል ለአዲስ ስልታዊ የትብብር ምዕራፍ ጠንካራ መሰረት መጣሉን ገልፀዋል።
ኤምባሴው ለኢቢሲ በላከው መረጃ በስብሰባው ውይይቶቹን ወደ ተጨባጭ ተግባራት ለመቀየር የሚያስችል ማዕቀፍ ለመቅረጽ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቋል።
#ebcdotstream #EBC #Pakistan #Ethiopia