Search

የህዳሴው ግድብ አፍሪካውያን የራሳቸውን ሀብት በራሳቸው አቅም ማልማት እንደሚችሉ ያሳየ ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ሓሙስ ነሐሴ 22, 2017 179

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለምረቃ መብቃቱ አፍሪካውያን የራሳቸውን ሀብት በራሳቸው አቅም ማልማት እንደሚችሉ ያሳየ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለፁ።

ቃል አቀባዩ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ፤ በደቡብ ሱዳን ጉብኝት ያደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ ከሀገሪቱ መንግስት ጋር መግባባት የተደረሰበት ውይይትም አካሂዷል ብለዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ቀጣናዊ ትስስርና ትብብር የመፍጠር ቁርጠኝነትን ያሳየ መሆኑን ገልፀዋል።

ከሳምንት በኋላ ኢትዮጵያ ትላልቅ ጉባኤዎችን ታስተናግዳለች ያሉት ቃል አቀባዩ፤ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችም በመጠናቀቅ ላይ ናቸው ብለዋል።

ከሳምንታት በኃላ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ካረቢያን ማህበረሰብ ጉባኤ የሀገራት መሪዎች በተገኙበት እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ህዝቦች ነፃነት ጉልህ ሚና የተጫወተች ሀገር እንደመሆኗ በካረቢያን ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ታሪክ አላት ነው ያሉት።

ጉባኤው ለአፍሪካዊያንና ዘረ አፍሪካዊያን የማካካሻ ፍትህን ለመሻት አህጉራዊ አጋርነት በሚል ለሶስት ቀናት እንደሚከናወንም አንስተዋል።

ሌላኛው በአዲስ አበባ የሚካሄደው ጉባኤ ደግሞ ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ሲሆን ከ25 ሺ በላይ ታዳሚዎች እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል ብለዋል ቃል አቀባዩ።

በዚህ ጉባኤም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየተገበረች ያለውን ተግባራዊ ምላሽ የምታጋራበት እንደሆነና የፋይናንስ አጋርነት የሚጠናከርበት ነው ሲሉ ቃል አቀባዩ ነብያት ጌታቸው ገልፀዋል።

አዲስ አበባም የስብሰባ ማዕከል ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ትስስር የሚፈጠርባት የአፍሪካ መዲና ጭምር እየሆነች መጥታለች ነው ያሉት።

ቃል አቀባዩ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ መግለጫቸውም አፍሪካዊያን የራሳቸውን ሀብት በራሳቸው አቅም ማልማት እንደሚችሉ ያሳየ ነው ብለዋል።

የቅኝ ግዛት እሳቤዎች በዚህ ዘመን ፍፁም ቦታ አይኖራቸውም ሲሉ ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።

በይመር አደም

#ebc #ebcdotstream #MFAEthiopia #GERD