አሐቲ እና ኢዮአስ ይባላሉ፤ ከተወለዱበት ጊዜ አንስቶ በነበረባቸው የልብ ህመም ምክንያት ቤተሰቦቻቸው የልጆቻቸውን ነገ ለማየት በተለያዩ ቦታዎች ሲያሳክሟቸው ቆይተዋል።
የልብ ህመም አሳሳቢ እና አብዛኛውን ጊዜም ውስብሰው በመሆኑ በሀገር ውስጥ የሚደረገው ሕክምና ብቻ መፍትሄ ሊገኝ አላስቻለም ነበር።
እናም ህፃናቱ በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል ውስጥ በሚሰጠው ነፃ የህክምና አገልግሎት እና በበጎ አድራጊዎች አጋርነት ወደ እስራኤል ተጉዘው ነፃ የልብ ሕክምና ማግኘት ችለዋል።
ገና የቀናት እድሜ ብቻ ባስቆጠረችበት ወቅት የልብ ህመም ያጋጠማት አሐቲ ከ 10 ዓመታት ስቃይ በኋላ በደጋግ ልባሞች መልካም ተግባር መዳኗን እናቷ ዘበናይ ነግረውናል።
እዚህ በነበራት ቆይታም ሆነ በእስራኤል በተደረገላት ሕክምና ወቅት የነበረው የሀኪሞች የኃላፊነት ስሜት ይሄ ነው የሚባል አይደለም ይላሉ እናት።
ዛሬ የመከራው ጊዜ አልፎ አሐቲ በቅን ልባሞች ታክማ እንደጓደኞቿ ሁሉ እሷም እንደልቧ ስትስቅ እና ስትጫወት ማየት በምን ቃል ይገለጻል? በማለት እናት በደስታ ጥያቄ በፈገግታ ይገልጹታል።
አሐቲም ከህመሟ መዳን በላይ የሐኪሞች እንክብካቤ እና ፍቅር ሞያቸውን እንድታከብር ብቻ ሳይሆን ስራቸው ህልሟ ሆኖ "እኔም ሳድግ ዶክተር ሆኜ ልቦችን አክማለው" ስትል ነው የነገረችን።
ልክ እንደ አሐቲ ሁሉ ህፃን ኢዮአስ ካጋጠመው የልብ ህመም በእስራኤል በተደረገለት ነፃ ሕክምና አገግሞ ተመልሷል።
ገና ወደምድር ከመምጣቱ የልብ ህመም የፈተነው ህፃን ኢዮአስ ነገ ላይ የሚናገረውን መልካም ሰብዓዊ ተግባር ገና በህጻንነቱ እየተመለከተ ነው።
ኢዮአስ ተጨማሪ ሕክምናዎች ቢቀሩትም አሁን ላይ ከህመሙ ስቃይ እና መጨነቅ ተገላግሎ ማየቷ እረፍትም ተስፋም እንደሆነላት እናቱ ፅዮን ገልጻልናለች።
በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል ላለፉት 36 ዓመታት ከ9 ሺህ በላይ ለሆኑ ታካሚዎች የነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎቶችን ሰጥቷል። ተቋሙ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚመጡ ሁሉን ያካተተ የልብ ሕከምና አገልግሎት ከክፍያ ነጻ ሕክምና በመስጠት ላይም ይገኛል።
በሴራን ታደሰ