Search

ኢትዮጵያ ባለራዕይ መሪ አላት - አሊኮ ዳንጎቴ

ሓሙስ ነሐሴ 22, 2017 231

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና በኢትዮጵያ ብልፅግናን እውን ለማድረግ በስፋት ግብርና ላይ እየሠሩት ያለው አስደናቂ ሥራ ባለራዕይ መሪ መሆናቸውን ማረጋገጫ ነው ሲሉ ናይጄሪያዊው ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ ተናገሩ፡፡

ሚስተር ዳንጎቴ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት በተፈረመበት ወቅት ንግግር አድርገዋል፡፡

ስምምነቱን አስመልክተውም እንደተናገሩት እስከ 3 ሚሊዮን ቶን ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያን ማምረት የሚያስችል አቅም ያለው ኢንቨስትመንት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ይህ የምርት መጠን ሀገር ውስጥ ከሚያስፈልገው ፍጆታ እጅግ የላቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ ፕሮጄክቱ ዳንጎቴ ግሩፕ በናይጄሪያ ውስጥ እያመረተ ካለው የዩሪያ ማዳበሪያ መጠን ጋር የሚስተካከል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም ፕሮጀክቱን ከዓለማችን የዩሪያ አምራች ፋብሪካዎች በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚያስቀምጠው መሆኑንም አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቂ የዩሪያ ማዳበሪያ ጥሬ ዕቃ የሚሆን የተፈጥሮ ጋዝ እንዳላት እና ይህም ለማዳበሪያ ፋብሪክ ፕሮጀክት ጥሩ መዳረሻ እንድትሆን እንዳስቻላት ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰጡት ብቁ አመራር ወሳኝ እንደሆነ ነው ሚስተር ዳንጎቴ የጠቀሱት፡፡

"ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና በኢትዮጵያ ብልፅግናን እውን ለማድረግ በስፋት ግብርና ላይ እየሠሩት ያለው አስደናቂ ሥራ ባለራዕይ መሪ መሆናቸውን ማረጋገጫ ነው" ብለዋል፡፡ 

የአፈር ማዳበሪያ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ዩሪያ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ዓይነት ማዳበሪያዎችን ስለሚያመርት ኢትዮጵያ ከራሷ ፍጆታም አልፋ ወደ ውጭ እንደምትልክም ገልጸዋል፡፡

ዳንጎቴ ግሩፕ በኢትዮጵያ ውስጥ የሲሚንቶ ፋብሪካም እንዳለው ጠቅሰው፣ ይህን የማዳበሪያ ፋብሪካም የበለጠ ለማስፋፋት ይሠራል ብለዋል፡፡

"መልካሙ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥሩ አጋሮቻችን ስለሆኑ በያንዳንዱ ፕሮጀክት ውስጥ ለበርካቶች ዕድል እንፈጥራለን" በማለት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን የጠቀሱት፡፡

የውጭ ሀገር ዜጋ የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ ከመሰረቱ እንደማይቀይር የጠቀሱት ሚስተር ዳንጎቴ፣ "እኔ የውጭ ሀገር ሰው ሳልሆን አፍሪካዊ ስለሆንኩ ኢትዮጵያ ቤቴ ነች" በማለት ለኢትዮጵያ ዕድገት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡

በለሚ ታደሰ

#ebc #ebcdotstream #ኢትዮጵያ #PMO #Fertilizer #AbiyAhmedAli #DangoteGroup