Search

ፋብሪካው ኢትዮጵያ ለማዳበሪያ ግዢ የምታወጣውን ብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ያስቀራል - አቶ አሕመድ ሺዴ

ሓሙስ ነሐሴ 22, 2017 281

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል በተደረሰው ስምምነት የሚገነባው የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ ከውጭ የሚገዛን ማዳበሪያ በማስቀረት ብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪን እንደሚያስቀር ገለፁ፡፡

ይህ ማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ በጎዴ ከተማ የሚቋቋም ሲሆን በሶማሊ ክልል በካሎብና ኢላላ ያለውን ተፈጥሮ ጋዝ በመጠቀም እንደሚገነባ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ይህ ፋብሪካ ማዳበሪያን በማምረት ለሀገር ውስጥ የሚያቀርብ ሲሆን ወደፊት አቅሙን እያሳደገ ሲሄድ ወደ ሌሎች ሀገራት ኤክስፖርት ማድረግ ይችላልም ብለዋል፡፡

የግብርና ዘርፉን ለመደገፍ ማዳበሪያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ እየገዛን ነው ምናስገባው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህ ፋብሪካ ይህን የሚያስቀር እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው ከማዳበሪያ ማምረት በተጨማሪም የተፈጥሮ ጋዝን በማልማት በግብርና፣ በማዕድን እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ትልቅ እንደሚኖረውም አቶ አሕመድ ሺዴ ጠቁመዋል፡፡

ይህ የማዳበሪያ ፋብሪካ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት በማፋጠን ረገድ ሚናው የጎላ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድልን ለመፍጠር እና ልማትን ለማነቃቃት የሚያግዝም ነው ብለዋል፡፡

የግብርና ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያግዘው ይህ ፋብሪካ ኢትዮጵያን በቀጠናው የማዳበሪያ አቅርቦት ማዕከል ሆና እንድትወጣ የሚያግዝ ነው ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ፋብሪካ ምክንያት በጎዴና በአካባቢዋ በርካታ መሰረተ ልማቶች ይገነባሉ ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህም የከተማዋን ዕድገት የሚያሳድግ ይሆናል ብለዋል፡፡

ባላፉት ሰባት ዓመታት ትላልቅ ሀገራዊ አቅምን የሚፈጥሩ ኢንቨስትመንቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ሰፊ ጥረት ሲደረግ ነበር ያሉት አቶ አህመድ ሽዴ፤ አሁን ይህ ጥረት ውጤታማ እየሆነ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ እንደዚህ አይነት ፋብሪካዎች በሀገር ውስጥ መገንባታቸው ኢትዮጵያ በቀጠናው ያላትን የኢኮኖሚ አቅምን እንደሚያሳድጉ ገልፀዋል፡፡

ፋብሪካው 2.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚፈስበት ሲሆን በአመት እስከ ሶስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የማምረት አቅም ያለው በአለም ከግዙፎቹ ፋብሪካዎች ተርታ የሚመደብ ነው፡፡

በሐይማኖት ከበደ

#Ethiopia #AbiyAhmedAli #DangoteGroup #Fertilizerfactory #AhmedShide