በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት መፈረሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ አድርገዋል።
ይህ ስምምነት ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ታላቅ የምስራች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዓመት 3ሚሊየን ቶን የአፈር ማዳበሪያ ማምረት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በቅርቡ የሚጀመር ሲሆን በ40 ወራት የሚጠናቀቅ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት።
ፕሮጀክቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቋቋመ ኮሚቴ የሚመራ ሲሆን፤ ይህም በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ትጋት ለመምራት እንዲቻል ታሳቢ ተደርጎ መቀረጹን ነው የጠቆሙት።
ከመጀመሪያው ዕለት አንስቶ በከፍተኛ ሥነ-ምግባር እና ቁጥጥር፤ ሥራውን በማከናወን በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ከሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች መካከል ይህ ፕሮጀክት አንዱ እንደሆነም አንስተው፤ ይህን መሰል ፕሮጀክቶችን እየለዩ በጥንቃቄ እንዲሁም በጥናት ላይ ተመስርቶ ማከናወን እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የማዳበሪያ ፋብሪካውን ልክ እንደ ሌላኛው ሕዳሴ የምናየው ሜጋ ፕሮጀክት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያን አቅም ካለችበት ከፍ ከሚያደርጉ ሥራዎች መካከል አንዱ መሆኑንም ነው ያነሱት።
በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉን አካታች የኢኮኖሚ ዘርፍ ለማነቃቃት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የግብርናው ዘርፍ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተው በግብርናው ዘርፍ ዋናው ግብዓት የሆነው ማዳበሪያ ከውጭ በመግባቱ በሚኖረው የማጓጓዝ ሒደት ከፍተኛ ችግር ነበር ብለዋል ፡፡
የግብርና ምርት መመረት በሚገባው ልክ ማምረት እንዳይቻል ከፍተኛ ጫና እንደነበረ አንስተው፤ ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ ማምረት እንዲሁም በሀገር ውስጥ ገንዘብ መገበያየት መቻል የኢትዮጵያን አርሶ አደሮች የረዥም ጊዜ ጥያቄ የሚመልስ ነው ብለዋል።
ለሌሎች የአፍሪካ ወንድሞቻችን ምሳሌ በመሆን፤ አፍሪካ የምትለምን፣ የምትራብ፣ የምትሰደድ ሳትሆን እራሷን የምታለማ እራሷን የምትመግብ እንዲሁም ለሌሎች የምትተርፍ የነገዋ አህጉር እንድትሆን ፈር የሚቀድ ጉዳይ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።