የአዲስ አበባ ከተማ በዓይነቱ የመጀመሪያ በሆነው እና "ብሉምበርግ ኢኒሽዬቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ" ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ላይ ባዘጋጀው ፍጥነትን ማሰተዳደር ዓለም አቀፍ ውድድር የወርቅ ሽልማት አሸናፊ ሆነች።
አዲስ አበባ ከተማ ለሽልማት ከታጩ ስምንት ከተሞች መካከል አንደኛ በመውጣት ነው የወርቅ ተሸላሚ የሆነችው።
ከውድድሩ መስፈርቶች መካከል የመንገድ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት እና የትራፊክ ደኅንነትን በመጠበቅ ረገድ ከተሞች ሥራ ላይ የሚያውሏቸው ስትራቴጂዎች ተግባራዊነት ተጠቃሽ ናቸው።
በዚህ መሰረት አዲስ አበባ ከተማ በፍጥነት እያስመዘገበችው ባለው ለውጥ እነዚህን መስፈርቶች አሟልታ በመገኘቷ ተሸላሚ መሆኗን ነው ከከንቲባ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ የሚያመላክተው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ “ብሉምበርግ ፍላንተሮፒስ ኢንሼቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ባዘጋጀው የመንገድ ደኅንነትን ማስተዳደር ላይ ከተማችን ባስመዘገበችው ተጨባጭ ውጤት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወርቅ ሽልማት አሸናፊ በመሆኗ ታላቅ ክበር ተሰምቶናል" በማለት በሽልማቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ዕውቅናው ከተማዋ ፍጥነትን ለማስተዳደር እና የመንገድ ደኅንነት ለማሻሻል እየወሰደች ያለውን ጠንካራ ቁርጠኝነት ዳግም የሚያረጋገጥ እንደሆነም ነው ከንቲባዋ የጠቀሱት።
በዕውቅናው የተገኘው የ100 ሺህ ዶላር ሽልማት፤ በቀጣይ የከተማዋ መንገዶች ደኅንነታቸው የተጠበቀ፣ ጤናማ፣ ለነዋሪው ተስማሚ፣ ምቹ እና አካታች እንዲሆኑ የሚያስችሉ የማሻሻያ ሥራዎችን ለመሥራት ተጨማሪ እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
የብሉምበርግ ኤል.ፒ. እና የብሉምበርግ ግብረ-ሠናይ ድርጅት መሥራች፤ የዓለም ጤና ድርጅት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እና ጉዳቶች አምባሳደር እንዲሁም የኒው ዮርክ ከተማ 108ኛው ከንቲባ የሆኑት ማይክል አር ብሉምበርግ፥ በፍጥነት ማሽከርከር በሀገራቸው በየዕለቱ 1 ሺህ 600 ሰዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ተናግረዋል።
"ብሉምበርግ ኢኒሽዬቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ" በዓለም ላይ ባሉ ሀገሮች ውስጥ ካሉ አጋር ድርጅቶች ጋር ሕይወትን ለማዳን ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል በትብብር በመሥራት ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ደኅንነት ምክር ቤት የአምስት ዓመት ስትራቴጂ አውጥቶ የመንገድ ደኅንነትን ለማሻሻል እየሠራ ይገኛል።
በዚህም የከተማ ውስጥ አጠቃላይ የፍጥነት ገደብ በሰዓት ቢበዛ 50 ኪሎ ሜትር ሲሆን በትምህርት ቤቶች፣ መኖሪያ አካባቢዎች፣ ገበያ ቦታዎች እና ሌሎች ለትራፊክ ግጭት ተጋላጭ በሆኑና በሚጨናነቁ አካባቢዎች ደግሞ ከ30 ኪ.ሜ በሰዓት ያነሰ እንዲሆን ተደርጓል።
በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደረገው የመንገድ ደኅንነት ውድድር አዲስ አበባ እና የኮሎምቢያዋ ቦጎታ የወርቅ አሸናፊዎች ሲሆኑ፣ የህንዷ ቤንጋሉሩ፤ የአርጀንቲናዋ ቦነስ አይረስ እና የሜክሲኮዋ ጓዳላጃራ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የብር ተሸላሚዎች መሆናቸው ታውቋል።
በሶስተኛ ደረጃ የኡጋንዳዋ ካምፓላ፣ የኬንያዋ ሞምባሳ እና የእኳዶሯ ኪቶ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሐስ ሽልማት የተበረከተላቸው ሀገራት ናቸው።