Search

ቻይና የሩሲያው ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን በሚገኙበት ወታደራዊ ሰልፍ ልታካሂድ ነው

ዓርብ ነሐሴ 23, 2017 728

ቤጂንግ - ቻይና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ እና ጃፓን ላይ የተቀዳጀችውን ድል 80 ዓመት ለማክበር ታላቅ ወታደራዊ ሰልፍ ልታካሂድ መሆኑ ተሰምቷል

በዚህ ታሪካዊ ክስተት ላይ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላዲሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡንን ጨምሮ 26 የውጭ ሀገራት መሪዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ወታደራዊ ትዕይንት ቻይና፣ ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካ የሚመራውን ዓለም አቀፍ ትብብር ለመቃወም የጋራ ግንባር እየፈጠሩ መሆኑን የሚያሳይ ነው ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ

በተለይም ኪም ጆንግ ኡን 2019 ከጎበኙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቻይናን የሚጎበኙ ሲሆን፣ በብዙ የውጭ ሀገር መሪዎች በተገኙበት ትልቅ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ሲታዩም የመጀመሪያቸው ይሆናል።

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ የሰሜን ኮሪያው መሪ በአሜሪካ፣ በደቡብ ኮሪያ እና በጃፓን መካከል ያለውን ትብብር ለመመከት ሲሉ ከቻይና እና ሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ያላቸውን ፍላጎት ማሳያ ነው።

በተለይም ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ በመላክ ተጨማሪ ገንዘብ የምታገኝ በመሆኑ በአሜሪካ ላይ የተጣለባትን ማዕቀብ ማንሳት አፋጣኝ ፍላጎቷ እንዳልሆነ ይታመናል።

በሰልፉ ላይ ከሚገኙት ሌሎች ታዋቂ መሪዎች መካከል ከጃፓን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀቶያማ ዩኪዮ እና ከቻይና ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው እንደ ኢራን፣ ቤላሩስ እና ሰርቢያ ያሉ ሀገራት መሪዎች ይገኙበታል።

በአንጻሩ፣ አብዛኛዎቹ የምዕራብ ሀገራት መሪዎች በሥነ-ሥርዓቱ ላይ አይገኙም ተብሏል። ይህ ሰልፍ ቻይና ወታደራዊ ኃይሏን የምታሳይበት እና ከቅርብ አጋሮቿ ጋር ያላትን ወዳጅነት የምታጠናክርበት አጋጣሚ እንደሚሆን ይጠበቃል

በሰለሞን ገዳ