አፍሪካ በየዓመቱ ከ6 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ ማዳበሪያ ከውጭ እንደምታስገባ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህ ጥገኝነት የግብርና ምርታማነትን ያዳክማል፤ አርሶ አደሮችንም ለዓለም አቀፍ የአቅርቦት መስተጓጎል ተጋላጭ ያደርጋል ይላሉ የግብርና ባለሙያዎች።
የፖለቲካ ግጭቶች ወይም ወረርሽኞች በሚከሰቱበት ወቅት ደግሞ የዓለም አቀፍ አቅርቦት ሰንሰለቶች ሲስተጓጎሉ፣ የማዳበሪያ ዋጋ እና አቅርቦት ከፍተኛ መለዋወጥ ሊያሳይ ይችላል። ይህ ደግሞ በቀጥታ የሰብል ምርትን እና የምግብ ዋስትናን ይጎዳል።
ምንም እንኳን አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ከውጭ በሚገባ ማዳበሪያ ላይ ጥገኛ ቢሆኑም፣ አህጉሪቱ ከምታስገባው መጠን በዘለለ ከፍተኛ የማዳበሪያ ምርት ወደተለያዩ አህጉራት ትልካለች።
ለአብነት እ.አ.አ. በ2021 የአፍሬክሲም ባንክ የንግድ ሪፖርት እንዳመለከተው፣ አፍሪካ ከ3.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማውጣት ማዳበሪያ ያስገባች ሲሆን ፣ ወደ ውጭ ማዳበሪያ በመላክ ደግሞ የ8.9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት ትርፋማ ሆናለች።
ይህ ትርፍ በዋነኛነት የተመሰረተው በሰሜን አፍሪካ በሚገኙ እንደ ሞሮኮ እና ግብፅ ባሉ ሀገራት ላይ ነው። እነዚህ ሁለት ሀገራት ብቻ ከአጠቃላይ የአህጉሪቱ የወጪ ንግድ ከ70 በመቶ በላይ ድርሻ አላቸው።
የአፍሪካ የንግድ እምቅ አቅም
እ.ኤ.አ. በ2021 ብቻ 15 የአፍሪካ ሀገራት የአፈር ማዳበሪያ ወደ ውጭ መላክ የቻሉ ሲሆን፣ ይህም በአህጉሪቱ ውስጥ ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ ትልቅ አቅም መኖሩን ያሳያል።
ሆኖም እንደ ኢትዮጵያ፣ ኮትዲቯር፣ ዛምቢያ እና ኬንያ ያሉ ትላልቅ የገብርና ምርት ሀገራት አሁንም በከፍተኛ ደረጃ ከውጭ በሚገቡ ማዳበሪያዎች ላይ ጥገኛ ናቸው።
የዚህ ጥገኝነት ዋና ምክንያት የአፈር ማዳበሪያ የምርት አቅም እጥረት ሲሆን፣ ይህንን ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነባው የዳንጎቴ ማዳበሪያ ፋብሪካ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ወሳኝ መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ።
ኢትዮጵያ ከናይጄሪያው ዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በ2.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ስምምነት ደርሳለች ። ይህ ፋብሪካ በሶማሌ ክለል በጎዴ፣ ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገነባ ሲሆን፣ በየዓመቱ 3 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ የማምረት አቅም ይኖረዋል ተብሏል።
የፕሮጀክቱ ዓላማ እና ጥቅሞች
ይህ ትልቅ ኢንቨስትመንት የአፍሪካን ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የምግብ ዋስትናን ለማሳደግ ያለመ ነው።
የማዳበሪያው ምርት በአካባቢው የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ በመጠቀም የሚመረት ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ለአካባቢው ኢኮኖሚ ትልቅ ጠቀሜታ አለው።
በፕሮጀክቱ ስምምነት መሰረት፣ የዳንጎቴ ግሩፕ 60 በመቶ ድርሻ ሲይዝ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) ደግሞ ቀሪውን 40 በመቶ ድርሻ ይይዛል።
ይህ ፕሮጀክት የአፍሪካ የምግብ ምርት አቅምን በማሳደግ፣ የዋጋ ንረትን በመቀነስ እና የአርሶ አደሮችን ኑሮ ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የዘርፉ ምሁራን እየገለጹ ይገኛል።
በሰለሞን ገዳ