በቅርቡ በቻይና ቤጂንግ ዋና አደባባይ በሚካሄደው ወታደራዊ ትርዒት ላይ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እንደሚገኙ ተዘግቧል።
አሁን ጥያቄው የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የመጓጓዣ ምርጫቸው ምንድነው? የሚለው ነው።
ኪም ጆንግ ኡን እ. አ. አ 2023 በሩቅ ምስራቅ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከተገናኙ በኋላ ይህ የመጀመሪያው የባህር ማዶ ጉዟቸው ይሆናል።
በቻይና ያደረጉት የመጨረሻ ጉብኝት ደግሞ ከስድስት ዓመታት በፊት እ.አ.አ በ2019 ነበር።
ከዚህ ቀደም ባለው መረጃ መሰረት የሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ መሪዎች ዓለም አቀፍ ጉዞዎችን ለማከናወን በአብዛኛው ባቡርን ይመርጣሉ።
በተለይ የኪም አባት ኪም ጆንግ ኢል ምንም አይነት የአየር በረራ ያላደረጉ ሲሆን፤ በአንድ ወቅት ወደ ሞስኮ በሚወስደው የባቡር ሀዲድ ላይ ሲጓዙ ከ10 ቀናት በላይ ያሳለፉበት አጋጣሚ ነበር።
በአንፃሩ ኪም ጆንግ-ኡን ከአባታቸው በተቃራኒ ከበረራ ሙሉ በሙሉ ከመቆጠብ ይልቅ ባለፉት ጊዜያት አነስተኛ አውሮፕላኖች ሲያበሩ የሚያሳዩ ምስሎችን የሀገሪቷ መገናኛ ብዙሃን አስተላልፈዋል።
እ.ኤ.አ በግንቦት 2018 ደግሞ ኪም ጆንግ ኡን "ቻማኢ-1" የተባለውን የራሳቸውን ጄት ተጠቅመው ቻይናን የጎበኙ ሲሆን አውሮፕላኑ የድሮ የሶቪየት ዘመን ሞዴል በመሆኑ ብዙ የደህንነት ጥያቄ አስነስቷል።
ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በተወያዩበት የሲንጋፖር ጉባዔ ደግሞ የቻይናን አውሮፕላን ተጠቅመው ተጉዘውም ነበር።
ከዚያ በኋላ ግን፣ ለዋና ዋና ጉዞዎቻቸው ኪም ባቡርን ወደ መጠቀም ተመልሰዋል።
ለምሳሌ እ.አ.አ. በ2019 ከትራምፕ ጋር በቬትናም ሃኖይ በተደረገው ሁለተኛው የመሪዎች ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከ60 ሰዓት በላይ በባቡር ተጉዘዋል።
አሁን ላይ ኪም ጆንግ ኡን ልክ እንደ አባታቸው ባቡሩ የሁልጊዜ ምርጫችው ሆኗል።
የኪም ባቡር ከውጭ ሲታይ ተራ ባቡር ይምሰል እንጂ በጣም የተጠናከረ ደህንነት ያለው መሆኑ ይነገራል።
በውስጡ የሳተላይት መገናኛዎች፣ የኮንፈረንስ እና የግል ክፍሎች እንዲሁም የአጃቢ መኪናዎችን ይዟል።
በውስጡ ያለው የተሟላ የጦር ትጥቅ ባቡሩን ከመደበኛ ባቡር የበለጠ አስተማማኝ ያደርገዋል ተብሏል።
ይሁንና የፕሬዚዳንት ኪም ጉዞን ለመተንበር አስቸጋሪ መሆኑን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በሴራን ታደሰ