Search

ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ድል የተቀዳጀችበት የኢትዮጵያዊያን የአንድነት ውል ማሰሪያ “ታላቁ የሕዳሴ ግድብ”

ዓርብ ነሐሴ 23, 2017 440

 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ድል የተቀዳጀችበት መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል እና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ አባል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ተናገሩ።

ኢቢሲ የዛሬይቱ ኢትዮጵያፕሮግራሙ "የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዲፕሎማሲ ጉዞ" በሚል ርዕስ ምሁራን እና ለሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሰፊ ውይይት አደርጓል።

በዚህ ፕሮግራም ላይ ጽሑፍ ያቀረቡት አምባሳደር ዘሪሁን አበበ እንዳሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተሠርቶ እስኪጠናቀቅ ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ተግዳሮቶች እንደገጠሙት እና ኢትዮጵያ ሁሉንም በፅናት እንዳለፈቻቸው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሌለችበት ነገር ግን ግብፅ የፈረመቻቸው የቅኝ ግዛት ውሎች ከተግዳሮቶቹ መካከል ናቸው ያሉት አምባሳደር ዘሪሁን፥ እነዚህ ውሎች እየተጠቀሱ ኢትዮጵያ ዓባይን እንዳትጠቀም መሰናክል ሆነው እንደነበረ ጠቅሰዋል።

"የውኃ ክፍፍል" በሚል አካሄድ በተፈረሙት የቅኝ ግዛት ውሎች ምክንያት፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እንኳን ለኢትዮጵያ ብድር እንዳይሰጡ "ከሌሎች ጋር ተስማምታችሁ " የሚል ሰንካላ ምክንያት ያቀርቡ እንደነበር ገልጸዋል።

ይህ ሁሉ ደግሞ ግብፅ እና ሱዳን ውኃውን ተከፋፍለው የኢትዮጵያን እና የሌሎች የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን የበይ ተመልካች ያደረገ እንደነበረም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ 13 ዓመታት ታግላ ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የናይል የትብብር ማዕቀፍ እንዲፈረም ማድረጓን ያወሱት አምባሳደሩ፥ በዚህም ኢትዮጵያ ታላቁን የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶችን በመሥራት የትብብር ማዕቀፉን ተግባራዊነት ማረጋገጧን ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደሚጀመር ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ የነበረው ፈተና እጅግ ከባድ የነበረ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ግን በአቋሟ ፀንታ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማዕከል አድርጋ ግድቡን መገንባቷን ተናግረዋል።

በተደረገው ጠንካራ ጥረትም ግብፅ እና ሱዳንን ያካተተ የመሪዎች መግለጫ ስምምነትን እንዲቀበሉ እና ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ጥናት እንዲያደረግ የተቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ግብፅ እና ሱዳን የግድቡን ግንባታ የብሔራዊ ደኅንነት አጀንዳ አድርገውት የነበረ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ግን አሁንም የቴክኒክ ጉዳይ እንደሆነ እና በገለልተኛ ባለሙያዎች የሚጠና መሆኑን በማሳመን ጥናቱ መካሄዱን አውስተዋል።

ንግግሩ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ የሄደበት መንገድንም አንስተው፤ በዚያ ደረጃም አሜሪካ የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ ብትሞክርም ኢትዮጵያ ግን በፅኑ አቋሟ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ መድረክ እንደመለሰችው ተናግረዋል።

ጉዳዩ በአፍሪካ ሕብረት አጀንዳነት እንዲቀጥል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(/) ራሳቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ለወቅቱ የሕብረቱ ሊቀመንበር ሲሪል ራማ ፎሳ በዝርዝር ማስረዳታቸውን ጠቅሰዋል።

በሁሉም ረገድ የሚያስኬዳትን ተጨባጭ ነገር ያጣችው ግብፅ፤ የግድቡን ጉዳይ አደገኛ ወደ ሆነው የተመድ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰዷን አስታውሰው ኢትዮጵያ ግን ጉዳዩን ተከታትላ ማክሸፏን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በኢ-መደበኛ ግንኙነቶችም ችግሩን በንግግር ለመፍታት ብትሞክርም ግብፆች ግን ለማንኛውም ዓይነት ንግግር ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ነው አምባሳደር ዘሪሁን የጠቀሱት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(/) ግብፅ ድረስ ሄደው የዓባይ ጉዳይ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ቢያረጋግጡም፤ ግብፅ ግን በምንም መልኩ ጉዳዩን በቀና መንፈስ ልትቀበል እንዳልቻለች አውስተዋል።

ግብፅ ይህን ሁሉ ጥረት የምታደርገው ለቀላል የውኃ አጠቃቀም ጉዳይ እንዳልሆን የጠቀሱት አምባሳደር ዘሪሁን፣ የኢትዮጵያ ውኃዋን በፍትሐዊነት መጠቀም ለሀገረ መንግሥቷ መረጋጋት አስተዋጽኦ ያደርጋል ብላ ስለምትሰጋ ነው ብለዋል።

ግብፅ እና አጋሮቿ ኢትዮጵያ ላይ ጫና የሚያበዙት ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር የነጠላትን ውኃዋን ከተጠቀመች፤ በቀጣናው የበለጠ ተፅዕኖ ፈጣሪ ትሆናለች ብለው ስለሚፈሩ እንደሆነም ተናግረዋል።

ስጋታቸው የአንዱ የታላቁ ኢትዮጵያ ግድብ እንዳልሆነ እና ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ የምትሠራቸው የውኃ ፕሮጀክቶች በልማቷ ላይ የሚያመጣው ጉልህ ለውጥ እንደሆነም ነው አምባሳደር ዘሪሁን የጠቀሱት።

በለሚ ታደሰ