በወላይታ ሶዶ ከተማ በሕገ-ወጥ መንገድ ለግለሰቦች ሊተላለፍ የነበረ 35 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ማዳን መቻሉን የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማ አስተዳደሩ የቆዩ የሕዝብ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጿል።
የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ጊዜያት የተከናወኑ ልማታዊ ሥራዎችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
የከተማዋ ከንቲባ እታገኝ ኃይለማርያም፥ በተለይ ከባለይዞታዎች እና ባለይዞታ ልጆች ጋር ተያይዞ ሲነሳ የነበረው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ፤ በተገቢው መንገድ የማጣራት ሥራ ተሠርቶ ምላሽ ማግኘቱን በመግለጫው ጠቅሰዋል።
በዚህም ያለአግባብ በግለሰቦች እጅ ሊገባ የነበረ 35 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል። የመሬቱ ልኬት ወደ ገንዘብ ሲተመን 35 ቢሊዮን ብር እንደሚሆንም አስረድተዋል።
14.2 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን አስፋልት መንገድ በፌደራል መንግስት ድጋፍ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመው፤ የዲችና ካልቨርት ሥራ ሂደት ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።
ይህ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ከንቲባዋ፥ በተመሳሳይ በኢንቨስትመንት ስም ቦታ ከወሰዱ 116 ባለሀብቶች መካከል 19ኙ ያለምንም ልማት እንቅስቃሴ አጥረው ማስቀመጣቸውን ገልፀው፣ ባላለሙት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳልም ነው ያሉት።
የከተማ አስተዳደሩ ለመልካም አስተዳደር እና ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በሰጠው ትኩረት መነሻ የመታሰቢያ ሀውልቶች ግንባታን ከማስቀጠል ባሻገር 6.2 ኪሎ ሜትር አዲስ የኮሪደር ልማት ሥራ ለማስጀመር ማቀዱንም ተናግረዋል።
በተመስገን ተስፋዬ