ኢ-ሰብዓዊ ተግባር በመፈፀም ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ያጓደሉ የፖሊስ አባላትን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
ሁለት የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባላት ህገ- ወጥ ድርጊት ሲፈፀም የተገኘ ግለሰብን በቁጥጥር ስር ለማዋል ባደረጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ድርጊቱ ሊፈፀም መቻሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልፀዋል፡፡
ተጠርጣሪው ከፖሊስ ለማምለጥ ባደረገው ግብግብ የፖሊስ አባላቱ ግለሰቡን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ለመውሰድ የሞከሩበት መንገድ ከሙያዊ ኃላፊነት ያፈነገጠ እና የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ መርህን ያልተከተለ መሆኑን ኮማንደሩ ተናግረዋል፡፡
ይህን ድርጊት የፈፀሙት ሁለቱ የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
የፖሊስ አመራርና አባላት የተጣለባቸውን ሙያዊ ኃላፊነት ሲወጡ የሰዎችን ሰብዓዊ መብት ባከበረ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የስነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ ፖሊሶች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
የፖሊስ አባላቱ ኢ-ሰብዓዊ ተግባር ሲፈጽሙ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወር እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በሜሮን ንብረት
#ebc #ebcdotstream #police #aapolice