ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰጡት በሳል አመራር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለውጤት እንዲበቃ ማስቻሉን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ መቻልን ያሳየችበት፤ ስህተታችንን ያረምንበትም ጭምር ነው ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰጡት በሳል አመራር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለውጤት እንዲበቃ አስችሏል ብለዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለውጤት መብቃት የአይቻልም ስሜትን የቀየረ የኢትዮጵያዊያንን የመልማት መሻት ጥያቄ የመለሰ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረው በኢህአዴግ ጊዜ እንደነበር አስታውሰው፤ ከመጀመር ባለፈ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ማስቀጠልና መፈጸም ሌላ ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከለውጡ በፊት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በብቃት የመምራት ችግርና ሙስና እንደነበር የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ለችግሮች እልባት መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ከለውጡ በፊት በገጠመው ችግር ረጅም ጊዜ መውሰዱን ጠቅሰው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አመራር ግድቡ ለውጤት እንዲበቃ አስችሏል ብለዋል፡፡
ከለውጡ በኋላ ግድቡ በአግባቡ እንዲካሄድ የተሰጠው ትኩረት እና ክትትል የግድቡ ግንባታ ለውጤት እንዲበቃ ማድረጉንም አስረድተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የለውጡ መንግስት ለሰጠው በሳል አመራር ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #GERD