በአለማችን ብዙ የዩቱዩብ ሰብስክራይበር ያለው ሚስተር ቢስት 426 ሚሊየን የዩቱዩብ ሰብስክራይበር በመያዝ ተወዳዳሪ የለውም።
እ.አ.አ. ግንቦት 7 1998 ካንሳስ ውስጥ የተወለደው አሜሪካዊው ዝነኛ ዩቲዩበር ጂሚ ዶናልድሰን የመጀመሪያ የዩቲዩብ ቪዲዮውን የሰራው የ13 አመት ታዳጊ እያለ ነበር።
ሆኖም የእውቅና ማማ ላይ ወጥቶ ታዋቂ ለመሆን ብዙ ዓመታትን ፈጅቶበታል። ጂሚ ዶናልድሰን፤ አሁን ላይ ከዩቲዩበርነቱ ባልተናነሰ በበጎ ምግባሩ የሚጠቀስ የ27 አመት ወጣት ነው።
በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ የሚሰራው ሚስተር ቢስት፤ በስሙ የሚጠራ የበጎ አድራጎት ተቋም አማካኝነት እስካሁን ከ50 ሚሊየን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ ወጭ በማውጣት የተለያዩ መልካም ተግባሮችን አከናውኗል።
ኮምፒውተሮችንና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ያሟሉ ትምህርት ቤቶችን ለወጣቶች የሚሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ሆስፒታልና የጤና ተቋማትን ገንብቷል።
አሜሪካንን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ለሚገኙ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ሰዎች አስር ሚሊየን የምግብ እርዳታ ለግሷል።
"የተቀናጡ ግዙፍ ቪላዎችን ከመግዛትና ሚሊዮን ዶላሮች የሚያወጡ አስር መኪኖችን ከመቀያየር ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችሉ የዩቲዩብ ቪዲዮዎችን መስራት እንደሚመርጥ የሚናገረው ዶናልድሰን፤ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ተግባር ለማዋልና የደግነት እጁን ለመዘርጋት ውቅያኖስ አያግደውም።
በደቡብ አሜሪካ፣ በእስያ፣ በአፍሪካ እና በተለያዩ አህጉራት የልግስና እጁ ደርሷል። በዚህ የበጎ አድራጎት ስራው በአፍሪካ በተለያዩ ሀገራት ራሱ በአካል እየተገኘ ለመጠጥ የሚሆን የውሀ ጉድጓድ አስቆፍሯል።
በዚህም መሰረት በካሜሮን፣ ዙምባብዌ፣ ኡጋንዳና ኬንያ ውስጥ ለሚገኙ የገጠር ከተሞች ለዓመታት የሚያገለግሉና ግማሽ ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አንድ መቶ የውሀ ጉድጓዶችን አስቆፍሮ ለአካባቢው ነዋሪዎች አስረክቧል።
በዚህ ወቅት በአንድ የኬንያ የገጠር መንደር በተገኘበት ወቅት ለደህንነት አስጊ የሆነ አሮጌ የእንጨት አስፈርሶ ዘመናዊ ድልድይ ገንብቷል። በኤልሳልቫዶር፣ ጃማይካ እና አርጀንቲና ውስጥ ለሚገኙ ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች አንድ መቶ ቤቶችን ገንብቶ የቤት እቃዎችን አሟልቶ ሰጥቷል።
አሜሪካና በተለያዩ ሀገራት ለሚኖሩ ሶስት ሺህ የአካል ጉዳተኞች ሰው ሰራሽ እግር እንዲያገኙ አድርጓል፤ በደቡብ አፍሪካም ወላጆቻቸውን ላጡ ልጆች ቤት ሰርቶ ሰጥቷል።
በህንድ በዐይን በሽታ እይታቸውን ላጡ አንድ ሺህ ሰዎች ሙሉ የዓይን ቀዶ ህክምና ወጭ በማውጣት እይታቸው እንዲመለስ ያደረገ ሲሆን፤ በፊሊፒንስ የመስማት ችግር ለነበረባቸው ሰዎች ቀዶ ህክምና ወጪ በማድረግ ጤናቸው እንዲመለሱ አድርጓል።
የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ አብረውት ከሚሰሩ ተቋማት ጋር በመሆን በተለያዩ ሀገራት 23 ሚሊየን ችግኞችን ተክሏል። በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የባህር ዳርቻዎችን በማፅዳት 33 ሚሊየን ፓውንድ የሚመዝኑ የተጣሉ ፕላስቲኮችንና ቆሻሻዎችን ማጽዳት ችሏል።
እድሜውን በሙሉ በዚህ መሰል የበጎ አድራጎት መቀጠል እንደሚፈልግ የሚናገረው ሚስተር ቢስት፤ በሰብስክራይበር ብዛት ተወዳዳሪ በሌለው የዩቲዩብ ቻናሉ በ2024 ከዩቲዩብ ብቻ 85 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት የቻለ ሲሆን፤ የሀብቱ መጠንም አንድ ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የቅርብ ጊዜ የፎርብስ ዘገባ አስታውቋል።
በዋሲሁን ተስፋዬ