ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን እና የሽብር ተግባራትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎች "ዋነኛ ተጠቂም ሆነ ቁልፍ አጋር" ህብረተሰቡ በመሆኑ የወንጀል ድርጊቶችን ለመዋጋት የዜጎች ትብብር ወሳኝ መሆኑን የፋይናንስ ደኅንነትን አገልግሎት ገለፀ።
የኢትዮጵያ ፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሌን ጊዜወርቅ በተለይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም እንዳሉት፥ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ከኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ ባሻገር ግጭቶችንና ሽብርተኝነትን በመደገፍ ለሀገርና ለቀጣናው ደህንነት ቀጥተኛ ስጋት በመሆኑ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ልንዋጋው ይገባል።
የእነዚህ ወንጀሎች ዋነኛ ተጠቂ ህብረተሰቡ ነው፤ በመሆኑም ወንጀሎቹን በመከላከል ጥረትም ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል አቶ ብሌን።
ህብረተሰቡ ለሕግ አስከባሪ አካላት መረጃና ጥቆማ በመስጠት፣ በወንጀለኞች ላይ አንድ ወጥ አቋም በመያዝ፣ እንደ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የኮንትሮባንድ ንግድና ሙስና ያሉ ለትላልቅ የወንጀል መረቦች የገንዘብ ምንጭ የሆኑ ወንጀሎችን በንቃት በመከታተል ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
የፋይናንስ ወንጀልን ከመሰረቱ በመለየትና በመከላከል ሂደት ውስጥ የዜጎች ሚና የማይተካ ነው ብለዋል።
"ይህ መንግሥት ብቻውን ሊያሸንፈው የሚችል ትግል አይደለም ያሉት አቶ ብሌን፤ የግሉ ዘርፍም በዚህ ትግል ውስጥ አስፈላጊ አጋር መሆኑን አንስተዋል።
የዘንድሮው የግሉ ዘርፍ መድረክ በካፒታል ገበያ ላይ ያተኮረ ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በካፒታል ገበያ ዙሪያ የግልና የመንግሥት አጋርነት የምክክር መድረክ ተካሂዶ አጠቃላይ ስብሰባው ዛሬ ፍፃሜውን እንደሚያገኝ ገልፀዋል።
በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀልን መከላከልን ዓላማው አድርጎ በአዲስ አበባ ለቀናት ሲካሄድ የቆየው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት ጉባዔ ዛሬ ሲጠናቀቅ የቀጣናውን የጋራ ጥረት የሚመሩ ከፍተኛ የፖሊሲ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በላሉ ኢታላ
#Ethiopia #UNECA #ESAAMLG #moneylaundering