Search

ውትድርና ራሳቸውን ለሀገርና ለህዝብ አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኛ በሆኑ ዜጎች ላይ የተመሠረተ የከበረ ሞያ ነው፦ ሌተናል ጄነራል ሀጫሉ ሸለመ

ቅዳሜ ነሐሴ 24, 2017 201

የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት 10ኛ ዙር ምልምል ወታደሮችን አስመርቋል።

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በመከላከያ ሚኒስቴር የሰው ሀብት ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ሀጫሉ ሸለመ የውትድርና ሞያ ራሳቸውን ለሀገርና ለህዝብ አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ በሆኑ ዜጎች ላይ የተመሠረተ የከበረ ሞያ ነው ብለዋል።

የማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የውትድርና ሞያ ስልጠና የሚጀምርበት እንጂ ሁሉም ዕውቀት የሚጠናቀቅበት ባለመሆኑ ሁሌም በመማርና ራስን በማብቃት ለላቀ የግዳጅ አፈፃፀም መዘጋጀት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።

ሠራዊቱ በጠንካራ ዲሲፕሊን የታነፀ፣ የውስጥና የውጪ ጠላቶችን በብቃት የሚከላከል፣ በሁሉም ግዳጆች ላይ ድል አድራጊነቱን በተግባር ያስመሰከረ ኃይል ነው ብለዋል።

ተመራቂ ምልምል ወታደሮች የዚህ ግዳጁን በሕገ መንግሥታዊ መርህ የሚወጣ ጀግና ሠራዊት አካል በመሆንና ከዕለት ተለት ስምሪት ትምህርት በመውሰድ በአርዓያነት እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል።

የነቃና የተዘጋጀ ሠራዊት ከመዋጋቱ በፊት ጦርነትን ማስቀረት፤ ካልተቻለ ደግሞ ተዋግቶ ማሸነፍ  መለያው መሆኑን ያነሱት ሌተናል ጄነራል ሀጫሉ፤ ተመራቂዎች በስልጠና ያገኙትን ዕውቀት ከሠራዊቱ ነባር ልምድ ጋር  በማስተሳሰር ሁሌም ዝግጁ ሆኖ መገኘት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮ/ል አዲሱ ተርፋሳ፥ ትምህርት ቤቱ የኮንቲንጀንት ሰልጣኞችን ከማሰልጠን በተጨማሪ ምልምል ሰልጣኞችን ተቀብሎ በማብቃት ላይ ይገኛል ብለዋል።

10ኛ ዙር ምልምል ወታደሮችም በግንባታ ትምህርት፣ በአካል ብቃት ስልጠና፣ በመሳሪያ ተኩስ፣ በስልትና በልዩ ልዩ ትምህር ትልቅ አቅም እንዲፈጥሩ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያውያን አሻራ በሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ምረቃ ዋዜማ ላይ መከናወኑ ምረቃውን ለየት ያደርገዋል ያሉት አዛዡ፤ ተመራቂዎቹ የሚሰጣቸውን የትኛውንም ግዳጅ በላቀ ሁኔታ ለመፈፀም የሚያስችል ስልጠና የወሰዱ መሆናቸውን የናግረዋል።

በቴዎድሮስ ታደሰ

#EBCdotstream #Hurso #graduation #soldiers