"ሀገር ስትጣራ አለሁ ለማለት ትልቅ ትንሽ አይልም፤ ሁላችሁም ሀገራችሁን ውደዱ፤ በቻላችሁት ልክ ሀገራችሁን ጥቀሙ"፦ የያኔዋ የ7 ዓመት አዳጊ - ሰሚራ ኢብራሂም
ሰኔ 15 ቀን 2007 ደበብ ወሎ ከላላ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ሀገር መልዕክት ልካላቸው ተስብስበዋል።
ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሀሉም የአቅሙን እያዋጣ ነው። የዚህ ታሪክ ተቋዳሽ ለመሆን የሚሽቀዳደሙ እግሮች ከየጎጆው በብዛት እየተመሙ ይገኛሉ።
እነ አቶ ኢብራሂም ቤትም ምን እናድርግ? ምን እንስጥ? ብለው ምክር ይዘዋል።
ፈንጠር ብላ ራሷ ካረባቻቻው እና መሬት እየጫሩ ከሚገኙ ሦስት ዶሮዎች አጠገብ የተቀመጠችው አዳጊ፣ “እኔ ዶሮዬን እሰጣለው” አለች። ቤተሰቡ ሁሉ በግርምት ተመለከቷት።
“ልጅ መሆኔን አትመልከቱ፤ ከነዚህ ሦስት ዶሮዎቼ መካከል ይህን ትልቁን (ገዘፍ ያለውን አውራ ዶሮ እየጠቆመች) ለሕዳሴ ግድብ መስጠት አፈልጋለው። ግድቡ እኮ የሁላችንንም ድጋፍ ይፈልጋል። ደግሞም ተማሪዎች በየአገሩ በአቅማቸው ቦንድ እየገዙ እንደሆነ ሰምቻለሁ። እኔም ለኢትዮጵያ ይህን ባደርግላት ደስታዬ ነው” ስትል ደፈር ብላ ተናገረች።
አባቷ በደስታ እቅፍ አድርገው ሳሟት። ቤተሰቡ ሁሉ መረቃት።
የያኔዋ የ7 ዓመቷ አዳጊ ሰሚራ ኢብራሂም በደስታ እየተፍነከነከች፣ እሷን ለማከል ጥቂት የሚቀረውን ግዙፍ አውራ ዶሮ ይዛ በፍፁም ቸርነት የሕዳሴ ዋንጫ ተቀምጦ ድጋፍ ወደሚሰበሰብበት ስፍራ ሄደች።
በገቢ ማሰባሰቢያው የታደሙት በአዳጊዋ አድራጎት ተገረሙ። “ይህ ዶሮ እዚሁ በጨረታ ይሸጥ” ተባለ።
ሁሉም ለአሸናፊት ተረባረበ። በመጨረሻው ዶሮው 17 ሺህ ብር በጨረታ ተሸጠ። በገንዘቡ ልክ በስሟ ቦንድ ተገዛላት።
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ አሻራዋን አኖረች። የከለላ ሕዝብ መዳፏን እየሳመ አመሰገናት፤ በምርቃት አረሰረሳት።
ዘመን ተሻጋሪው ግድብ ላይ በልጅነቷ አሻራዋን ያኖረችው ሰሚራ ኢብራሂም ዛሬ 17 ዓመት ሆኗታል።
ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 አግኝቶ የሕዳሴ ግድብ ለዚህ ደረጃ በመብቃቱ ምን ተሰማሽ? ብሎ ጠይቋታል።
“ፈጣሪ ዕድሜ ሰጥቶኝ ይህን ስላሳየኝ በጣም ደስ ብሎኛል። ደስታዬን ለመግለፅ ቃላት የለኝም። ወደፊትም ገና ብዙ መልካም ነገሮች እንደምናይ አምናለሁ” ብለዋለች።
“በእርግጥ የእኔ ብቻ አይደለም፤ በሁላችን ርብርብ ነው ግድቡ እዚህ የደረሰው። ሁሉም የቻለውን ያደረገለት ግድብ ነው።” ስትል የኢትዮጵያውንን የትብብር መንፈስ ገልጻች።
“ለሀገር መሥዋዕት ለመክፈል ትልቅ ትንሽ አይልም፤ ሁላችሁም ሀገራችሁን ውደዱ፤ በቻላችሁት ልክ ሀገራችሁን ጥቀሙ።” ስትልም መልዕክቷን አስተላልፋለች።
ሰሚራ የእርሷ ትውልድ ምልክት ናት፤ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ እንዳረፈበት ኅያው ምስክር ሲቆጠር፣ ከእርሷ ነው የሚጀመረው።
በዮናስ ወልደየስ
#EBC #ebcdotstream #GERD #resilience #unity #hope #brightfuture